የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ፣ ቢያንስ አምስት ሰዎችን የገደለውንና በርካታዎችን ያቆሰለውን የሩሲያ የድሮን ጥቃት “ሽብርተኝነት” ሲሉ ኮንነዋል።
ጥቃቱ የተፈጸመው በሰዎች በተጨናነቀ የመንገደኞች ባቡር ላይ መሆኑን የአካባቢው ባለስልጣናት ገልጸዋል።
ባለፈው ማክሰኞ በሰሜን ምስራቅ ዩክሬን ካርኪቭ ግዛት ውስጥ፣ አንደኛው የባቡር ክፍል (carriage) በድሮን ሲመታና ሌሎች ሁለት ድሮኖች ደግሞ አቅራቢያው ላይ ሲፈነዱ ከ200 በላይ ሰዎች በባቡሩ ውስጥ ነበሩ፤ዘለንስኪ እንደተናገሩት ጥቃቱ በደረሰበት የባቡር ክፍል ውስጥ 18 ሰዎች የነበሩ ሲሆን፣ ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ ለማድረግ ምንም ዓይነት “ወታደራዊ ምክንያት” የለም ብለዋል።
እስካሁን ሩሲያ ስለ ጥቃቱ የሰጠችው ምንም አይነት አስተያየት ባይኖርም በታሪክ አስከፊ በሆነው በዚህ የክረምት ወቅት በዩክሬን የኃይል እና የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶች ላይ የምታደርሰውን የድሮን እና የሚሳኤል ጥቃት አጠናክራ ቀጥላለች።
በደቡባዊቷ የባህር ወደብ ከተማ ኦዴሳ በደርዘን የሚቆጠሩ ድሮኖች ጥቃት ያደረሱ ሲሆን፣ የሦስት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ሌሎች በርካቶች ቆስለዋል። የአካባቢው ባለስልጣናት በአንድ የኃይል ተቋም ላይ “ከፍተኛ ጉዳት” መድረሱንም ገልጸዋል።
በዋና ከተማዋ አቅራቢያ በሚገኝ የመኖሪያ መንደር ላይ በደረሰ ጥቃት ደግሞ ባልና ሚስት ሲገደሉ፣ የአራት ዓመት ልጃቸው ቆስሏል።በሩሲያ ጥቃት ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዩክሬናውያን ያለ ሙቀት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል እና ውሃ ለመኖር እንደተገደዱ የቢቢሲ ዘገባ ያሳያል፡፡
ዘለንስኪ በማህበራዊ ድረ-ገጽ ባስተላለፉት መልዕክት፣ “በየትኛውም ሀገር ቢሆን በሰላማዊ ሰው ባቡር ላይ የሚሰነዘር የድሮን ጥቃት እንደ ሽብርተኝነት ነው የሚቆጠረው” ብለዋል። የዩክሬን የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ያወጣው ምስልም አንደኛው የባቡር ክፍል በእሳት ሲቃጠል ያሳያል።
ሩሲያ የዕለት ተዕለት የአየር ጥቃቷን የቀጠለችው፣ ባለፈው ሳምንት ጦርነቱን ለማቆም ያለመ የሰላም ንግግር በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መካሄድ በጀመረበት ወቅት ነው። ንግግሩ በአሜሪካ አደራዳሪዎች የታገዘና “ተስፋ ሰጪ” ተብሎ የተገለጸ ቢሆንም፣ አሁንም በይዞታ ግዛቶች ላይ ያሉ አለመግባባቶች አልተፈቱም። በዚህ ሳምንት መጨረሻ ተጨማሪ ስብሰባዎች ይደረጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡
ሀና ሰይፉ
ጥር 20/2018 ዓ.ም
