በድርቅ በተመታው በሰሜን ምስራቅ ኬንያ የሚገኙ ነዋሪዎች፤የሞቱ ከብቶቻቸውን ወደ ሩቅ ሜዳዎች እየጎተቱ ለማቃጠል ተገደዋል ተብሏል።
በኢትዮጵያና በሶማሊያ ድንበር የምትገኘው የማንዴራ ግዛት ካለፈዉ ዓመት ግንቦት ወር ጀምሮ ምንም ዓይነት ዝናብ አላገኘችም።
ብሔራዊ የድርቅ አስተዳደር ባለሥልጣን ዘጠኝ ያህል ጋዛቶችን በማስጠንቀቂያ ደረጃ ላይ ያስቀመጠ ሲሆን፤በማንዴራ ያለው የአሳሳቢነት ደረጃ ግን ከአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አንድ ደረጃ ብቻ የሚቀረው ነው ብሏል።
በግዛቲቱ የሚገኙት አብዛኞቹ ነዋሪዎች አርብቶ አደሮች ሲሆኑ፤ ለኑሯቸውም በእጅጉ የሚተማመኑት በእንስሶቻቸው ላይ ነው።
ከጥቅምት እስከ ታህሳስ የሚጠበቀው አጭር ዝናብ ከመደበኛው በሁለት ሦስተኛ በመቀነሱ፤በ23 የኬንያ ግዛቶች ውስጥ የሚገኙ ከሁለት ሚሊየን በላይ ሰዎች እየተባባሰ ለመጣ የምግብ ዋስትና ዕጥረት ተጋልጠዋል።
የረሃብ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓተ መረብ በቅርቡ እንዳስታወቀው፤በኬንያ፣ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ ከ20 እስከ 25 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች ሰብዓዊ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፤ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ለዚህ የተዳረጉት በድርቁ ምክንያት ነው።
የኬንያ መንግሥትና እንደ ቀይ መስቀል ያሉ የረድዔት ድርጅቶች በቦቴ መኪና የውኃ ማከፋፈልን፣ የምግብ እርዳታንና የገንዘብ ድጋፍን አጠናክረው ቢቀጥሉም ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት ማሟላት እንዳልቻሉ ገልጸዋል ያለዉ አፍሪካ ኒዉስ ነዉ።
እስከዳር ግርማ
ጥር 20/2018 ዓ.ም
