አርሰናል ዛሬ ምሽት በኤምሬትስ የቻምፒዮንስ ሊግ የመጨረሻ ጨዋታውን ከካይራት አልማቲ ጋር በማድረግ ያጠናቅቃል፡፡
ለመሆኑ ለቻምፒዮንስ ሊጉ የመጀመሪያ ተሳትፎው የሆነውና ስሙም ለበርካታ የኳስ ቤተሰቦች እንግዳ የሆነው ይህ የካዛኪስታን ክለብ ማነው?
በመጀመሪያ በ1954 ሎኮሞቲቭ አልማ-አታ በሚል ስም የተመሰረተው ይህ ክለብ፤ በ1955 ኡሮዛይ ተብሎ ተሰይሞ ነበር። በመጨረሻም በ1956 “ጥንካሬ” ወይም “ሀይል” የሚል ትርጉም ያለውን ካይራት የሚለውን ስያሜ አገኘ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም በዚህ ስሙ ይታወቃል።
ክለቡ መቀመጫውን በሀገሪቱ ደቡብ ምስራቅ በምትገኘው አልማቲ ከተማ ያደረገ ሲሆን፣ ይህም ከአርሰናሉ ኤምሬትስ ስታዲየም ከ4,000 ማይሎች በላይ ርቀት ላይ ይገኛል።
“ሀሊቅ ኮማንዳሲ” (የሕዝብ ቡድን) የሚል ቅጽል ስም ያለው ካይራት፣ ቀድሞ በነበረው የሶቪየት ከፍተኛ ሊግ ውስጥ እስከ መፍረሱ ድረስ ይሳተፍ ነበር።
በሊጉ ያስመዘገበው ከፍተኛ ውጤት በ1973 ዓ.ም ለአራራት የሬቫን ተከታይ በመሆን ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ነው።
በ1988 ዓ.ም ኔፍትቺ ባኩን 4–1 በማሸነፍ የተባበሩት የሶቪዬት ሶሻሊስት (USSR) ፌዴሬሽን ዋንጫን አንስቷል።
እ.ኤ.አ በ1991 ሀገሪቱ ነፃነቷን ካገኘች በኋላ ካይራት የካዛክስታን ፕሪሚየር ሊግን ለአምስት ጊዜያት አሸንፏል።
የመጀመሪያውን የሊግ ዋንጫ በ1992 ያነሱ ሲሆን፤ ከ12 ዓመታት በኋላ በድጋሚ ድል ቀንቷቸዋል።
ከዚያ በኋላ ባሉት 16 ዓመታት ውስጥ ግን ክለቡ ከሊግ መውረድን፣ ለኪሳራ መቃረብን እና ወደ ከፍተኛው ሊግ መመለስን የመሰሉ ፈታኝ ጊዜያትን አሳልፎ በ2020 በድጋሚ የሊጉ ሻምፒዮን መሆን ችሏል።
በራፋኤል ኡራዝባክቲን የሚመራው ስብስብ በ2024 እና 2025 ተከታታይ የሊግ ዋንጫዎችን በማንሳቱ ለሻምፒዮንስ ሊግ የማለፍ ዕድል አግኝቷል።
በ2024 ያደረጉት ያልተሳካ ሙከራ ትዝታ በ2025 ተደምስሷል፤ ካይራት የስሎቪኒያውን ኦሊምፒያ ሉብሊያናን፣ የፊንላንዱን ኩፒኤስ (KuPS) እና የስሎቫኪያውን ስሎቫን ብራቲስላቫን ካሸነፈ በኋላ፣ ሴልቲክን በአስደናቂ ሁኔታ በመለያ የቅጣት ምት በመርታት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሻምፒዮንስ ሊግ ማለፍ ችሏል። ነገር ግን በደረጃ ሰንጠረዡ የመጨረሻውን ይዞ መሰናበቱን አስቀድሞ አረጋግጧል፡፡
ምስጋናው ታደሰ
ጥር 20/2018 ዓ.ም
