”የቸገረን የወልቃይት ጉዳይ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

ቀደም ሲልም የፌዴራል መንግሥት፤ የወልቃይት እና ሌሎች አወዛጋቢ ቦታዎችን ጉዳይ “በሕዝበ-ውሳኔ” ለመፍታት የሚያስችሉ ሂደቶችን እንደሚተገብር በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቢቆይም በትግራይ ክልል ባለሥልጣናት በተለይም በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱ የሚታወስ ነው።

የወልቃይት አካባቢ “በትግራይ ክልል ስር መሆን አለበት” የሚል አቋም የሚያራምደው ህወሓት፤ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት ከአካባቢው የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀዬአቸው ከመመለሳቸው በፊት የምዕራብ ትግራይ ዞን አካባቢውን ማስተዳደር እንዳለበት ይሟገታል፡፡

የአካባቢው አስተዳደር ጉዳይ በሕዝበ-ውሳኔ መፍትሔ ማግኘት እንዳለበት የሚገልጸው የፌዴራሉ መንግሥት ፤ ህወሓት “ተፈናቃዮችን መያዣ ማድረጉን” በመግለጽ ይከሳል።

በዛሬው እለት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀያቸው መመለስ እንደሚፈልጉ በመግለጽ ”ቀድመው የነበሩበት ከባቢም ይምጡልን ይላል፤ ማነው የያዛቸው ነው ጥያቄው” ብለዋል፡፡

ለምሳሌም በትግራይ ጦርነት ሲጀመር ከኢሉባቦር ተፈናቅለው ለሄዱ ሰዎች የአካባቢው ነዋሪ ማሳቸውን እየተንከባከበና እየሸጠ ለተፈናቃዮቹ በአካውንታቸው ገንዘቡን ሲያስገባ ነበር በማለት አሁን ላይ ተፈናቃዮቹ ከትግራይ ወደ ኢሉባቦር እንደተመለሱ ነው የገለጹት፡፡

”በራያ፣ በጸለምት፣ በብዙ የኦሮሚያ አካባቢዎች ሰዉ ተመልሶ እየኖረ መሆኑን አይታችኋል፤ የቸገረን አሁን ወልቃይት አካባቢ ነው” ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ”ልክ ገበሬ ዘር ዘርቶ ከዝናብ በኋላ ምርት እንደሚጠብቀው ስደት፣ መፈናቀል፣ ስቃይ ዘርተው ከሌሎች ሃይል እርዳታ የሚጠብቁ አሉ… የተፈናቀለን አትሔድም ብለው ይዘው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

”ተፈናቃይ ያልተመለሰበት አካባቢ ሰው እንዳይመለስ ስላልፈለገ ሳይሆን፤ ሰዎቹ መመለስ ስላልፈለጉ ሳይሆን ተፈናቃይን መያዣ ያደረገ ፖለቲካ ኢትዮጵያ ውስጥ በመኖሩ ነው” ብለዋል፡፡

”ልክ መንገድ ላይ ስትሄዱ የኔቢጤዎች ልጆቻቸውን መለመኛ እንደሚያደርጉት… አንዳንድ ፓርቲዎች ተፈናቃዮችን የራስ ህልውና ማቆያ ያደርጓቸዋል” ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ይሄን ለማሻሻል ብዙ ሙከራ ተደርጓል፤ ብዙ ስራ ተሰርቷል በማለትም አክለዋል፡፡

አዲስአለም አበበ

ጥር 26/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *