በምስራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከእስላማዊ መንግስት አይ ኤስ ቡድን ጋር ግንኙነት ያላቸው አማፂያን 66 ሰዎችን መግደላቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
በምስራቅ ኮንጎ ኢቱሪ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተልዕኮ ቃል አቀባይ፤ ከሲቪል ማህበረሰቡ በተገኘ መረጃ መሰረት የሟቾች ቁጥር ከ31 ወደ 66 ሲቪሎች ከፍ ብሏል ብለዋል።
ኤዲኤፍ የተባለው ቡድን በኮንጎ እና በኡጋንዳ የሚንቀሳቀስ የኡጋንዳ እስላማዊ ቡድን ነው።
የአካባቢው የሲቪል ማህበረሰብ ፕሬዝዳንት ማርሴል ፓሉኩ፤ ሴቶችን ጨምሮ ሁሉም ተጎጂዎች በገጀራ ተገድለዋል ብለዋል። የታገቱት ሰዎች ቁጥር ግን እስካሁን አይታወቅም።
ጥቃቱ ባለፈዉ እሁድ በኮንጎ እና በኡጋንዳ ጥምር ሃይሎች የተጀመረው ተጠናክሮ የቀጠለ የቦምብ ጥቃት ዘመቻ ግብረመልስ ሊሆን እንደሚችል ተጠርጥሯል።
በቅርብ ዓመታት ውስጥ የኤዲኤፍ ጥቃቶች በኮንጎ እና ኡጋንዳ ድንበር አቅራቢያ ተጠናክረው ወደ ምሥራቃዊ ኮንጎ ዋና ከተማ ወደ ጎማ እና ወደ አጎራባች ኢቱሪ ግዛት ተዛምተዋል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ ኤዲኤፍ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በመግደል እና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ህጻናት ጨምሮ በርካታ ሰዎችን በማገት ይከሱታል።
ባለፈው ታህሳስ ወር ኤዲኤፍ በሰሜን ኪቩ ግዛት በሚገኝ ሌላ መንደር ቢያንስ 10 ሰዎችን መግደሉ እና በርካታ ሰዎችን ማገቱ ይታወሳል ያለዉ አፍሪካ ኒዉስ ነዉ።
ሊዲያ ደሳለኝ
የካቲት 03/2018 ዓ.ም
