ሼክ ሻክቡት ቢን ናህያን አል ናህያን በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር፤‹‹ከአፍሪካ ጋር ያለን ግንኙነት በቀይ ባሕርና በህንድ ውቅያኖስ በኩል ላለፉት አሥርት ዓመታት በንግድ፣ በባሕር ትስስር እና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ላይ የተመሰረተ ነው።
ዛሬ ያ ታሪካዊ ትስስር እያደገ በመጣው ዲፕሎማሲያዊ አሻራችን እየተንፀባረቀ ሲሆን፤ ተጨማሪ ኤምባሲዎችን የመክፈት ሥራም በመከናወን ላይ ይገኛል። በተመሳሳይ በኤምሬትስ ውስጥ ያለው የአፍሪካ ዲፕሎማሲያዊ ውክልና እያደገ መምጣቱ፣ ሀገራችን ለአፍሪካ ንግድ፣ ፋይናንስና ውይይት ማዕከል የመሆን ሚናዋን ያጠናክረዋል››ብለዋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለአፍሪካ ኅብረት የ2063 አጀንዳ ግቦች ያላትን ድጋፍ እንዲሁም ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽንና ከአባል ሀገራት ጋር በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በታዳሽ ኃይል፣ በምግብ ዋስትና፣ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና በአቅም ግንባታ ዘርፎች ትብብርን ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት ታረጋግጣለች ነዉ ያሉት፡፡
በተባበሩት አረብ ኤምሬትስና በአፍሪካ መካከል ያለው ትብብር በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በሰብዓዊ ድጋፎችና በሌሎችም ውጤታማ አመላካቾች አማካኝነት እየተመራ ይገኛል።
በ2019 እና በ2023 መካከል የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በመላው አፍሪካ ከ1መቶ10 ቢሊየን ዶላር በላይ ኢንቨስት ለማድረግ ቃል ገብታለች፤ ይህም በዚያ ወቅት በማንኛውም ነጠላ ሀገር የተመዘገበ ከፍተኛው የኢንቨስትመንት ደረጃ ነበር፡፡
ከዚህ ካፒታል ውስጥ ከ70 ቢሊየን ዶላር በላይ የሚሆነው ወደ ኢነርጂ፣ ለአከባቢ ተስማሚ እና ታዳሽ ዘርፎች የፈሰሰ ነው። ይህም የኃይል አቅርቦት ለኢንዱስትሪ መስፋፋትና ለኢኮኖሚ ብዝሃነት መሰረት መሆኑን የሚያሳይ የረጅም ጊዜ እይታን ያንፀባርቃል ተብሏል።
በአፍሪካ ግሪን ኢንቨስትመንት ኢኒሼቲቭ ስር የንፁህ ኢነርጂ ልማትን ለማፋጠን 4.5 ቢሊየን ዶላር የተንቀሳቀሰ ሲሆን፤ከ60 በላይ የፀሐይ፣ የንፋስ፣ የጂኦተርማል፣ የባትሪ ክምችት እና የግሪን ሃይድሮጅን ቴክኖሎጂ ፕሮጀክቶች በመዘጋጀት ላይ ናቸው።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከ9 የአፍሪካ ሀገራት (ናይጄሪያ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሴራሊዮን፣ ጋቦን፣ አንጎላ፣ ኬንያ፣ ኮንጎ-ብራዛቪል፣ ሞሪሸስ እና የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ) ጋር አጠቃላይ የኢኮኖሚ አጋርነት ስምምነቶችን አጠናቃለች የተባለ ሲሆን፤ እነዚህ ስምምነቶች የታሪፍ ቅነሳን ብቻ ሳይሆን አገልግሎቶችን፣ ዲጂታል ንግድን እና የኢንቨስትመንት ጥበቃንም የሚያካትቱ ናቸው።
ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ አጠቃላይ የውጭ ዕርዳታ ውስጥ ወደ 40 በመቶ የሚጠጋው ወይም በግምት 20.9 ቢሊየን ዶላር ወደ አፍሪካ ሀገራት የተላከ ሲሆን፤ ይህም የልማት፣ የሰብዓዊ እና የበጎ አድራጎት እርዳታዎችን ያጠቃልላል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከታህሳስ 2-4 2026 የሚካሄደውን የተባበሩት መንግሥታት የውሃ ኮንፈረንስ ከሴኔጋል ጋር በጋራ ታስተናግዳለች።
ሁለት የግሎባል ሳውዝ ሀገራት ይህንን ዓለም አቀፍ ሂደት በጋራ ሲመሩ የመጀመሪያው ሲሆን፤ ይህም በመላው አህጉሪቱ ዋነኛው የልማት ፈተና በሆነው የውሃ ደህንነትና የንፅህና አጠባበቅ ላይ መሻሻል ለማምጣት ያለውን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው መባሉን የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ኤምባሲ ለጣቢያችን በላከዉ መረጃ ላይ ተመልክተናል፡፡
የካቲት 09/2018 ዓ.ም
