የጅማ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ማዕከል በኢትዮጵያ አልፎም በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ የሚጠቀሱ የላቀ የህክምና አገልግሎቶችን በስፋት እየሰጠ መሆኑን አስታውቋል።
ማዕከሉ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል የካንሰር ህክምና በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ሲሆን፤ ከኬሞቴራፒ እና ራዲዮቴራፒ በተጨማሪ በቴክኖሎጂው የመጨረሻ የሆነውን “ብራኪ ቴራፒ አገልግሎት ለምዕራብ ኢትዮጵያ እና ለጎረቤት ሀገራት (ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን) ታካሚዎች እየሰጠ ይገኛል፡፡
በተጨማሪም ካንሰርን ጨምሮ መዳን ለማይችሉ ታካሚዎች ከህመም ነጻ ሆነው ቀሪ ጊዜያቸውን በክብር እንዲያሳልፉ የሚረዳ የፓሊያቲቭ ህክምና ማዕከል አቋቁሞ እየሰራ ነው፡፡
በካርዲዮሎጂ ዘርፍም ሆስፒታሉ ክፍት የልብ ቀዶ ህክምና አገልግሎትን መስጠት ከጀመረ ሰንብቷል ነው የተባለው።
በቴክኖሎጂ ረገድም የገጠር ታካሚዎች ወደ ከተማ መምጣት ሳይጠበቅባቸው ባሉበት ሆነው በልዩ ባለሙያዎች መታከም እንዲችሉ የሚያስችል የቴሌ ማዲስን አገልግሎት ከኦሮሚያ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ለመጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን የህክምና ማዕከሉ ክሊኒካል ዳይሬክተር ዶ/ር ሁንዴ አህመድ ገልጸዋል፡፡
ሆስፒታሉ አገልግሎቱን ዘላቂ እና ጥራት ያለው ለማድረግም ከመንግስት እና የግል አጋርነት አሰራርን በመከተል፤ በተለይም በፓቶሎጂ፣ በራዲዮሎጂ እንዲሁም በመድሃኒት አቅርቦት ላይ ከግል ባለሀብቶች ጋር በመስራት የ24 ሰዓት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የክሊኒካል ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
ሊዲያ ደሳለኝ
የካቲት 11/2018 ዓ.ም
