የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ከሶስት ዓመት ወዲህ የ1መቶ50 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተገለፀ

ከሶስት አመት በፊት ከ40 እስከ 45 ብር ይሸጥ የነበረው የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ እንደ አይነቱ እና ጥራት ልዩነት ከፍ ባለ ብር እየተሸጠ ነው ተብሏል።

የንፅህና መጠበቂያ በ6 ወራት ጊዜ ውስጥ እስከ 7 በመቶ ጭማሪ ያሳያል የተባለ ሲሆን፥ ይህ ጭማሪ ለንፅህና መጠበቂያዎች የተጋነነ መሆኑ ተገልጿል።

የዋጋ ጭማሪው አንድ ጊዜ ጥቅም ላይ በሚውለውም ሆነ በድጋሚ ጥቅም ላይ በሚውለው የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ላይ የሚስተዋል ነው።

ባለፈው አንድ አመት ጊዜ ውስጥ የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ አምራቾች ማህበር ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱ የተገለፀ ሲሆን፥ ማህበሩንም ሆነ የግል አምራቾችን እየፈተነ ያለው የታክስ ጉዳይ መሆኑ ተገልጿል።

ከኢትዮ ኤፍኤም ጋር ቆይታ ያደረጉት የማህበሩ ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ሚካል ማሞ፥ የዋጋ ንረቱ ከፍ ያለበትን ምክንያት ሲያስረዱ የጥሬ ዕቃ ዋጋ መጨመር አንዱ መሆኑን ገልፀዋል።

አንድ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውለው የንፅህና መጠበቂያ አብዛኛው ምርት ከውጭ የሚገባ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቷ፥ በድጋሚ አገልግሎት ላይ የሚውለውም ጥቂት ምርቶቹ ከውጭ የሚገቡ መሆናቸውን ነግረውናል።

ምርቱ ወደ አገር ውስጥ ሲገባም ሆነ ሲሸጥ ከታክስ ነፃ ቢደረግ ብዙ ችግሮችን ይፈታል ያሉ ሲሆን፥ ማህበሩንም ሆነ አምራቾቹን በከፍተኛ ሁኔታ እየፈተነ ያለው የታክስ ጉዳይ መሆኑን ገልፀዋል።

በፕሮጀክት ላይ ፕሮጀክት በስብሰባ ላይ ስብሰባ ይደረጋል እንጂ ተገቢውን ትኩረት አላገኘም ብለዋል።

ከመስከረም ወር ጀምሮ በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ በነፃ እንዲሰጥ የሚያዝ ሰርኩላር በትምህርት ሚኒስቴር በኩል መውጣቱ የተገለፀ ሲሆን፥ አስገዳጅ ለማድረግ ህጎች እየተዘጋጁ መሆኑ ተገልጿል።

የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ጉዳይ ከጤና ባለፈ የሴቶችን ስራ የማከናወን አቅም፣ የተማሪዎችን ትምህርት ውጤታማነት እና የሴቶችን ሰብአዊ ክብር የሚነካ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑ ተነስቷል።

ይህንን ጉዳይ የፈረንሳይ የልማት ተራድኦ ድርጅት ከሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ጋር በመተባበር የወር አበባ ጤና እና ንፅህናን በተመለከተ በመንግስት እና በግል ዘርፉ መካከል ባዘጋጀው  የውይይት መድረክ ላይ ሰምተናል።

እስከዳር ግርማ

የካቲት 12/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *