ተጠንቀቁ

በላስቲክ አፍን በመሸፈን የሚደረግ አደገኛና አሳሳች የክብደት መቀነሻ ዘዴ

በቻይና ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ወጣቶች አፋቸውን በቀጭን የላስቲክ መጠቅለያ በመሸፈን፣ ምግቡን በማኘክና በመቅመስ ብቻ መልሰው የሚተፉበት አዲስ የክብደት መቀነሻ ዘዴ በስፋት እየተሰራጨ ይገኛል።

“የአፍ መከላከያ” ተብሎ የተሰየመው ይህ ዘዴ ካሎሪ ወደ ሰውነት እንዳይገባ በመከልከል አዕምሮ ምግብ ያገኘ እንዲመስለው እና የጥጋብ ስሜት ለመፍጠር ያለመ ቢሆንም፣ የጤና ባለሙያዎች ግን ድርጊቱ ለከፋ የጤና ቀውስ እንደሚዳርግ ያስጠነቅቃሉ።

ይህ ተግባር አዕምሮ ከምግብ ጣዕም እና ይዘት ብቻ ደስታ እንዲያገኝ ስለሚያደርገው፣ ለከባድ የአመጋገብ መዛባት እንደ አኖሬክሲያ እና ቡሊሚያ ላሉ ችግሮች መንስኤ ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል።

ከዚህም ባለፈ ላስቲኩ በሚታኘክበት ጊዜ የሚፈጠሩ ጥቃቅን የፕላስቲክ ስብርባሪዎች ከምራቅ ጋር ተቀላቅለው ወደ መተንፈሻ እና የምግብ መፈጨት ሥርዓት ውስጥ በመግባት ለከፍተኛ የጤና መታወክ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል፡፡

ምንም እንኳን ይህ ድርጊት በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠር እይታ በማግኘት ትልቅ መነጋገሪያ ቢሆንም፣ ባለሙያዎች ግን ይህ ድርጊት ለሰውነት የሚያስፈልገውን ኃይል እንደማይሰጥና እንዲያውም ከጊዜ በኋላ የምግብ ፍላጎትን ይበልጥ ሊያባብስ እንደሚችል ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም መንጋጋን በመቆለፍ ምግብ መከልከል ያሉ መሰል አደገኛ የክብደት መቀነሻ ሙከራዎች ለሕይወት አስጊ በመሆናቸው፣ ህብረተሰቡ ከእንዲህ አይነት አሳሳች መረጃዎች ራሱን እንዲጠብቅ ባለሙያዎች አሳስበዋል ሲል ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል፡፡

ሐመረ ፍሬው

የካቲት 18/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *