የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር ከጦርነት ተመላሾች እና አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ሌሎች ላይ ለሚሰሩ 31 ተቋማት ድጋፍ አደረገ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢቲ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የሚውል የቁሳቁስ ድጋፍ የርክክብ መርሃ-ግብር ዛሬ  የካቲት 18 ቀን 2018 ዓ.ም አካሂዷል።

ዛሬ የተከናወነው ርክክብ፥አየር መንገዱ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣትና የወገኖቹን ህይወት በዘላቂነት ለመቀየር የጀመረው ጥረት አካል ነው ተብሏል።

ድጋፉ በአጠቃላይ 31 ማህበራትንና ተቋማትን ጨምሮ 4 ክልሎችን ተደራሽ ያደረገ ነው።

ድጋፉ የተደረገላቸው ተቋማት በጦርነት ሳቢያ ተፈናቅለው የተመለሱ ዜጎችን፣ የአካል ጉዳተኞችን፣ አረጋውያንን፣ የኦቲዝም ማዕከላትን እና የተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን ያቀፉ ናቸው።

መርሃ-ግብሩ በዋናነት ዜጎች በሀገሪቱ ውስጥ ምቹና የተረጋጋ ህይወት እንዲኖራቸው ለማድረግና ጠንካራ የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓት ለመዘርጋት ያለመ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተወካይ ባስተላለፉት መልእክት፥አየር መንገዱ የኢትዮጵያ ህዝብ ኩራት እንደመሆኑ መጠን፣ ከትርፍ በዘለለ ለህዝብ ወገንተኝነቱን በተግባር ማሳየት እንደሚገባው ገልጸዋል።

“ይህ ዛሬ የተደረገው ድጋፍ መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ አይደለም፤ በቀጣይም በሰፋና በተደራጀ መልኩ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በጋራ እንሰራለን” ብለዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፥ የተበረከተው ቁሳቁስ በትክክል ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች እንዲደርስ አስፈላጊው ክትትል እንደሚደረግ አረጋግጧል።

ሀና ሰይፉ

የካቲት 19/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *