በኢትዮጵያ በስማርት ስልኮችና በኢንተርኔት ተደራሽነት መስፋፋት ምክንያት ህፃናት ለከፍተኛ የ‹‹ኦንላይን››ጥቃት ተጋላጭ እየሆኑ መመጣቸውን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በሚኒስቴሩ የህፃናት ጥበቃ ስርዓት ማጎልበት ዴስክ ሃላፊ ወ/ ሮ ቃልኪዳን ሽመልስ እንደገለጹት፤ በተለይም እድሜያቸው ከ12 ዓመት በላይ የሆኑና የኢንተርኔት ተጠቃሚ የሆኑ ህፃናት በጥቃት አድራሾች ኢላማ እየሆኑ ይገኛሉ።
እንደ ሃላፊዋ ገለጻ፤ ጥቃት አድራሾች ህፃናትን በጓደኝነት፣ በቪዲዮ ጌሞችና በተለያዩ ስጦታዎች በማታለል የግል መረጃዎችንና ፎቶግራፎችን እንዲልኩ በማድረግ ለከፋ ጥቃት ያጋልጧቸዋል።
በተጨማሪም ህፃናት ስለ ኢንተርኔት ጉዳት ያላቸው እውቀት አነስተኛ መሆኑ እና ወላጆች ልጆቻቸው በቴክኖሎጂው ምን እንደሚሰሩ በቂ ክትትል አለማድረጋቸው ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡
ጥቃቶች ሚስጥራዊ ስለሚሆኑ በቁጥር ደረጃ መረጃዎችን ለማግኘት አሁንም ስራዎች እንደሚቀሩ የጠቆሙት ሀላፊዋ፤ይህንን ስር የሰደደ ችግር ለመፍታት ሚኒስቴሩ ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ ከዩኒሴፍና ከቻይልድ ፈንድ ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ በሚገኙ 20 ትምህርት ቤቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን፤ በየክልሎቹም ለፖሊስና ለፍትህ አካላት ስልጠናዎች እየተሰጡ ይገኛሉ።
ሀና ሰይፉ
የካቲት 19/2018 ዓ.ም
