እስራኤል ሰብዓዊ እርዳታ ቀስ በቀስ እንዲገባ ለማድረግ የጋዛን የዕርዳታ መስመር እንደገና እንደምትከፍት ተናግራለች፡፡
እስራኤል በኢራን ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች እና አሜሪካንና ሊባኖስን ባሳተፈው የቀጣናው ውጥረት መባባስ ምክንያት የተፈጠሩ የደህንነት ስጋቶችን ተከትሎ ዘግታው የነበረውን የከረም ሻሎም መውጫ፤ ሰብአዊ እርዳታ ቀስ በቀስ ወደ ጋዛ እንዲገባ ለማድረግ እንደገና እንደምትከፍት ገልጻለች።
እስራኤል እና ዩናይትድ ስቴትስ በኢራን ላይ ጥቃት መጀመራቸውን ተከትሎ የከረም ሻሎም መውጫ ቅዳሜ ዕለት ተዘግቶ ነበር፡፡
መውጫውን እንደገና የመክፈት ውሳኔ የተላለፈው በደህንነት ግምገማ መሠረት መሆኑን በፍልስጤም ግዛቶች ለሲቪል ጉዳዮች ኃላፊነት ያለበት የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር አካል ኮጋት አስታውቋል።
እስራኤል ቅዳሜ ዕለት በፍልስጤም ግዛት እና በግብፅ ድንበር ላይ የሚገኘውን ራፋህን ጨምሮ ወደ ጋዛ የሚወስዱ ሁሉንም መውጫዎች እንደ “ደህንነት” እርምጃ መዝጋቷን አስታውቃ ነበር።
በእስራኤል በኩል የማያልፈውና የጋዛ ነዋሪዎች ወደ ውጭው ዓለም የሚወጡበት ብቸኛው በር የሆነው የራፋህ መውጫ፤ የእስራኤል ጦር ከሀማስ ጋር በነበረው ጦርነት ወቅት ተቆጣጥሮት ከቆየ ከሁለት ዓመታት በኋላ፣ ለሰዎች እንቅስቃሴ የካቲት 2 ቀን እንደገና ተከፍቶ ነበር።
ሊዲያ ደሳለኝ
የካቲት 24/2018 ዓ.ም
