የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ አሜሪካ በህንድ ውቅያኖስ ላይ በኢራን የጦር መርከብ ላይ የፈጸመችውን ጥቃት “በባህር ላይ የተፈጸመ አሰቃቂ ድርጊት” ሲሉ አወገዙ።
ሚኒስትሩ አሜሪካ ለፈጸመችው ድርጊት “መራር ዋጋ ትከፍላለች” ሲሉ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ በማህበራዊ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ “ዴና” (IRIS Dena) የተሰኘችው የኢራን ፍሪጌት ወይም የጦር መርከብ ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ በአሜሪካ የባህር ውስጥ ሰርጓጅ መርከብ ጥቃት እንደደረሰባት ገልጸዋል።
መርከቧ ጥቃት የደረሰባት ከኢራን የባህር ዳርቻ 2 ሺህ ማይልስ ርቆ፣ በስሪላንካ አቅራቢያ በሚገኝ ዓለም አቀፍ የባህር ክልል ውስጥ መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
መርከቧ በወቅቱ የህንድ ባህር ኃይል እንግዳ ሆና በመንቀሳቀስ ላይ እንደነበረችና ወደ 130 የሚጠጉ መርከበኞችን አሳፍራ እንደነበርም ተገልጿል።
አራቅቺ አሜሪካ በወሰደችው በዚህ እርምጃ “መጥፎ አርአያነት” አሳይታለች ያሉ ሲሆን፣ “ቃሌን ያዙ፤ አሜሪካ ላስቀመጠችው ለዚህ አደገኛ ቅድመ ሁኔታ መራር ጸጸት ይገጥማታል” ሲሉ ዝተዋል።
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር (ፔንታገን) በበኩሉ ጥቃቱን ያረጋገጠ ሲሆን፣ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በአሜሪካ ሰርጓጅ መርከብ በቶርፒዶ ተመቶ የጠላት መርከብ ሲሰምጥ ይህ የመጀመሪያው መሆኑን አስታውቋል።
በዚህ ጥቃት ቢያንስ 87 የኢራን ባህር ኃይል አባላት መገደላቸው የተነገረ ሲሆን፣ ድርጊቱ በአሜሪካ፣ እስራኤል እና ኢራን መካከል እየተፋፋመ የመጣውን ቀጠናዊ ውጥረት ይበልጥ ይጨምራልም ተብሏል።
ልዑል ወልዴ
የካቲት 26/2018
