የአሜሪካ የደህንነት ተቋማት የኢራን መንግስት በሳይበር በኩል ጥቃት ሊሰነዝር እንደሚችል የሚገልጹ ተከታታይ የጥንቃቄ መልዕክቶችን ለግል ኩባንያዎችና ለመንግስት መስሪያ ቤቶች እያሰራጩ መሆኑ ተሰማ።
ሲ-ኤን-ኤን (CNN) የብሔራዊ ደህንነት ምንጮችንና የተሰራጩ የውስጥ ማስታወሻዎችን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው፤ ይህ ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው አሜሪካ ከቴህራን ጋር በገባችበት ጦርነት ሳቢያ ኢራን አጸፋዊ እርምጃ ልትወስድ ትችላለች በሚል ስጋት ነው።
በማስጠንቀቂያው መሰረት፤ ኩባንያዎችና የመንግስት ተቋማት ሊሰነዘርባቸው የሚችለውን ማንኛውንም አይነት የሳይበር ጥቃት ለመከላከል ዝግጁነታቸውን እንዲያጠናክሩና ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ታዘዋል።
በተለይም የኢነርጂ ተቋማት፣ የፋይናንስ ዘርፎች እና ከመከላከያ ጋር ግንኙነት ያላቸው ድርጅቶች የጥቃቱ ዋነኛ ኢላማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተመልክቷል።
ምንም እንኳን እስካሁን የተለየና በግልጽ የታወቀ የጥቃት ሙከራ ባይኖርም፤ የሀገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስቴር (DHS) እና ኤፍ-ቢ-አይ (FBI) የደህንነት ስጋቱ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፣ በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ የጸጥታ አካላት በንቃት እንዲከታተሉ አሳስበዋል።
የኢራን የሳይበር ጥቃት ስጋት ያየለው፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ወታደራዊ ውጥረት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመጣበትና የቀጠናው ሁኔታ ባልተረጋጋበት በዚህ ወቅት ነው።
ልዑል ወልዴ
መጋቢት 02/2018 ዓ.ም
