ጅቡቲ ላይ ተሽከርካሪዎች በብልሽት ወይም በአደጋ ሲወድቁ ለማስነሳት በትንሹ እስከ 1 ሚሊየን ብር እየተጠየቀ ነዉ ተባለ

ተሽከርካሪዉ ከጅቡቲ ወጥቶ ኢትዮጵያ ድንበር ላይ በሚደርስ ማንኛውም አደጋም ለጥበቃ በቀን ከ4 ሺህ እስከ 5 ሺህ ብር የፀጥታ ችግር ባለባቸዉ አካባቢዎች ደግሞ 10 ሺህ ብር ደረሰኝ የሌለዉ ክፍያ እየተጠየቀ መሆኑን ሰምተናል።

ይህንን የሰማነዉ በትናንትናው ዕለት የገቢ ግብር ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ ገንዘብ ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገዉ ዉይይት የደረቅ ጭነት ትራንስፖርት ዘርፍ ካሰማዉ ቅሬታ ነዉ።

በትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ዘርፍ ማህበር ከደረቅ ጭነት ትራንስፖርት ዘርፍ ተወካይ ሆነዉ የተገኙት እንቁጣጣሽ ፍቃዱ፤ የደረቅ ጭነት ትራንስፖርት እየገጠሙት ስላሉ ችግሮች በመድረኩ አብራርተዋል።

ተወካይዋ የጅቡቲ መንግስት ከራሱ አንድ በጣም ካረጀ ክሬን ዉጪ ከኢትዮጵያ ክሬን አስገብቶ መኪና ማንሳትም ሆነ ትቶ መዉጣት አይቻልም ብለዋል።

“ተሽከርካሪዎቹ ከወደቁበት አንስቶ ቀና አድርጎ ቁጭ ለማድረግ እንኳን ከ500 ሺህ 600 ሺህ ብር ነዉ የምንጠየቀዉ ለዚህ ደግሞ አግባብነት ያለዉ ደረሰኝ የለም” ሲሉ አብራርተዋል።

ሲቀጥሉም “ጀንደር መሪ” የሚሏቸዉ ይሄንን አገልግሎት የሚሰጡ አካላት የሚጠይቁት ገንዘብ ምናልባት ተሽከርካሪዉ ሁለት እና ሶስቴ ተመላልሶ እንኳን የሚያገኘዉ ገቢ አይደለም” ብለዋል።

የደረቅ ጭነት ዘርፍ ከአዲስ አበባ ተነስቶ የተለያዩ ሀገራት አቋርጦ ድንበር ተሻግሮ ነዉ ተመልሶ የሚመጣዉ ያሉት ተወካይዋ፤እንደ ምስራቅ አፍሪካ ቀጣና እንኳን ምንም አይነት ስርዓት የተዘረጋለት ዘርፍ አይደለም በማለት ገልፀዋል።

በሌላ በኩል ተሽከርካሪዉ ከጅቡቲ ወጥቶ በኢትዮጵያ ድንበር ለሚደርስበት ማንኛውም አደጋ አሁንም የጥበቃ ይጠየቃል ተብሏል።

እንቁጣጣሽ ፍቃዱ በመድረኩ እንደተናገሩት፤ ለደረቅ ጭነት ባለንብረቶች ለጥበቃ ለቀን ለብቻ ለማታ ለብቻ እየተጠየቅን ነዉ ሲሉም አንስተዋል።

እንደ ቀጣና የደረቅ ጭነት ትራንስፖርት ብቻ ሳይሆን የሎጀስቲክስ ስርዓቱ ትልቅ ትኩረት እና ክትትል የሚያስፈልገው ነዉ ሲሉ አፅንኦት ተሰጥተው ተናግረዋል።

ትናንት በተደረገዉ የገቢ ግብር ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ ዙሪያ በተደረገዉ ዉይይት የሂሳብ መዝገብ አያያዝን አስመልክቶ የተቀመጠዉ ድንጋጌ በተለያዩ ባለድርሻ አካላት ቅሬታን አስተናግዷል።

ለአብነትም ቅሬታዉን ያሰማዉ የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ዘርፉ ተወካይ የሆኑት እንቁጣጣሽ ፍቃዱ እንዳስረዱት የሂሳብ መዝገብ መያዝ ለዚህ ዘርፍ የማይፈለግ ሆኖ ሳይሆን በፍፁም የማይቻል ነዉ ብለዋል።

ይህንን በነባራዊ ሁኔታ ላይ በጥናት የተደገፈ መረጃ እና ማስረጃ ማቅረብ የሚቻልበት ነዉ ሲሉ ተናግረዋል።

ቁምነገር አየለ

መጋቢት 02/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *