ሚኒስትሩ መሐመድ ቢን አብዱላዚዝ ኳታር እና ኦማን ጥቃት እየተፈጸመባቸው ባለበት ሁኔታ አስታራቂ ሆነው ሊሰሩ አይችሉም ብለዋል።
የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ፤በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ግጭት እንዲረግብ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፥ ኢራን እና ዩናይትድ ስቴትስ በድርድር መፍትሄ ለማግኘት ወደ ውይይት ጠረጴዛው እንዲመለሱ አሳስበዋል።
ሚኒስትሩ መሐመድ ቢን አብዱላዚዝ ከአልጄዚራ ጋር በነበራቸው ልዩ ቆይታ፥ ኢራን በጎረቤቶቿ ላይ የምትፈጽመው ጥቃት ለማንም እንደማይጠቅም ተናግረዋል፡፡
ኢራን ከዩናይትድ ስቴትስ እና ከእስራኤል ለሁለት ሳምንታት ለደረሰባት የአየር ድብደባ በጎረቤቶቿ ላይ ሚሳዔሎችን እና ድሮኖችን በመተኮስ ጉዳት እንዳደረሰችና ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን በማበላሸት እና የቀጣናውን በሃይል የሚመራውን ኢኮኖሚ ክፉኛ በማወክ ምላሽ ሰጥታለች ብለዋል።
ሚኒስትሩ ኳታር በሲቪል መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸሙትን ጥቃቶች ጨምሮ በተስፋፋው ጥቃት በጣም እንደተጨነቀች ገልጸዉ፤ አሁን ያለንበት ሁኔታ አሳዛኝ ነው ብለዋል፡፡
ወደ ድርድር ጠረጴዛው ከመመለስ ውጪ ቀጣይነት ያለው እና ዘላቂ መፍትሄ በሌላ መንገድ የለም ብለን እናምናለን ሲሉ ለአልጄዚራ ተናግረዋል።
ኳታር ሉዓላዊነቷን በቀጥታ የሚነኩ እና ያላግባብ በኳታር መንግስት ላይ የተፈጸሙትን አስነዋሪ ጥቃቶች በፅኑ ታወግዛለች ብለዋል።
ዶሃ ይህንን ትንኮሳ ለመከላከል እና ራስን የመከላከል መብቷን ለመጠቀም ማንኛውንም ሊደረግ የሚችል እና ህጋዊ እርምጃ መውሰዷን ትቀጥላለች ሲሉ አክለዋል።
ሊዲያ ደሳለኝ
መጋቢት 02/2018 ዓ.ም
