በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚከሰተው የአየር ንብረት ለውጥና በረሃማነት በእናቶች ጤና እና ሞት ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን አንድ ጥናት ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ስነ-ተዋልዶ ጤና ሰጪ ድርጅቶች ህብረት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አበበ ከበደ በማሳያነት እንዳነሱት፤ በተለይም በሶማሌ እና በአፋር ክልሎች በሚታየው የውሃ እጥረት ምክንያት፣ ሴቶች አንድ ጀሪካን ውሃ ለማግኘት እጅግ ረጅም ርቀት በእግራቸው ለመጓዝ ይገደዳሉ።
ይህ ከፍተኛ አካላዊ ድካም በተለይ በነፍሰጡር እናቶች ላይ ከፍተኛ የጤና እክል ይፈጥራል።
ከዚህም በተጨማሪ በገጠራማ አካባቢዎች የሚገኙ የጤና ተቋማት የውሃ፣ የመብራት እና የመንገድ መሰረተ ልማት ያልተሟላላቸው መሆኑ ችግሩን አባብሶታል ብለዋል።
“ውሃ በሌለበትና መብራት በማይሰራበት የጤና ተቋም ውስጥ እናቶች ሲያረግዙና ሲወልዱ ለከፍተኛ የጤና እክልና ለሞት ይጋለጣሉ” ያሉት ዋና ስራ አስኪያጁ፤ የአየር ንብረት ለውጥ ፖሊሲዎች እነዚህን መሰረታዊ የማህበረሰብ ችግሮች ታሳቢ ያደረጉ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ሊዲያ ደሳለኝ
መጋቢት 02/2018 ዓ.ም
