ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ፤ዩክሬን ከኢራን የካሚካዜ ድሮኖች ራሳቸውን ለመከላከል የእሷን ሙያዊ ልምድ ለሚፈልጉ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ለምትሰጠው እርዳታ ምትክ ገንዘብ እና ቴክኖሎጂ ትፈልጋለች ብለዋል።
ዘሌንስኪ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ የባለሙያዎችን ግምገማ ለማካሄድ እና የድሮን መከላከያ ስራዎች እንዴት መከናወን እንዳለባቸው ለማሳየት ሶስት ቡድኖች ወደ መካከለኛው ምስራቅ ተልከዋል።
በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ቡድኖቹ ወደ ኳታር፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ሳውዲ አረቢያ እንዲሁም በጆርዳን ወደሚገኝ የአሜሪካ ወታደራዊ ካምፕ መላካቸውን ገልጸው ነበር።
‹‹ይህ በወታደራዊ ዘመቻዎች ውስጥ ስለመሳተፍ አይደለም፤ እኛ ከኢራን ጋር ጦርነት ላይ አይደለንም››ብለዋል ዘሌንስኪ።
ከባህረ ሰላጤው ሀገራት ጋር ይበልጥ መሰረታዊ እና የረጅም ጊዜ የድሮን ስምምነቶች ዙሪያ ሊደራደሩ እንደሚችሉ እና ዩክሬን ለምታደርገው እርዳታ ምትክ ምን እንደምታገኝ አሁንም ውይይት እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል።
‹‹ለእኛ ዛሬ ቴክኖሎጂውም ሆነ የገንዘብ ድጋፉ አስፈላጊ ናቸው›› ብለዋል ዘሌንስኪ።
የባህረ ሰላጤው ሀገራት የኢራንን የሻሄድ ድሮኖች ለመመከት ከፍተኛ መጠን ያለው የአየር መከላከያ ሚሳኤሎችን ተጠቅመዋል።
ኪቭ ግን በየምሽቱ የሩሲያን ድሮኖች የምትመታው ርካሽ እና ትናንሽ ድሮኖችን ጨምሮ በተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ነው።
ዘሌንስኪ እንደተናገሩት አሜሪካ እንዲሁም ከአውሮፓ፣ ከመካከለኛው ምስራቅ እና ከአፍሪካ የተውጣጡ ሀገራት እነዚህን ጥቃቶች እንዴት መከላከል እንደሚቻል ከዩክሬን እርዳታ ጠይቀዋል።
ሆኖም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ድሮኖችን ለመጣል የዩክሬን እርዳታ አያስፈልጋትም ብለዋል።
ሊዲያ ደሳለኝ
መጋቢት 07/2018 ዓ.ም
