ዩንቨርስቲዉ አካታች እና ፍትሃዊ የተማሪዎች የቅበላ መስፈርት መጠቀም እንዳለበት ተጠቁሟል።
የራስ ገዝነት ሽግግር ላይ የሚገኘዉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሁለት አመት ሽግግር ጊዜ ቢቀመጥለትም ሙሉ ለሙሉ ለመሸጋገር ከታቀደዉ ጊዜ በላይ መዉሰዱ ተነግሯል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰዉ ሃብት ልማት፣ ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የዩኒቨርስቲዉን የ 6 ወራት አፈፃፀም ሪፖርትን መገምገሙን ከምክር ቤቱ ያገኘነዉ መረጃ አመልክቷል።
የቋሚ ኮሚቴዉ ሰብሳቢ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ፤ ዩኒቨርስቲዎች ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተማሪዎችን መቀበል የሚያስችላቸውን አካታች እና ፍትሃዊ መስፈርት መጠቀም እንዳለበት ገልፀዋል።
በግምገማዉ ላይ የተገኙት የዩንቨርስቲዉ ኘሬዝደንት ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ እንደገለፁት፤ በመንግሥትም ይሁን በራሳቸው ከፍለው የሚማሩ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ከተቀረፁት 66 ፕሮግራሞች ውስጥ ከ20 በማይበልጡት ላይ ብቻ መማር እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
በህዳር ወር መጀመሪያ የዩንቨርስቲዉ ኘሬዝደንት በተቋማቸዉ ሰጥተዉት በነበረዉ ጋዜጣዊ መግለጫ የኘሮግራሞች ግምገማ መደረጉን ገልፀዉ ነበር።
ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በወቅቱ ተፈላጊም አስፈላጊም ናቸዉ የተባሉት በመለየት ከዚህ ዉስጥ ኢኮኖሚዉ የሚፈለገዉ የትኛዉ ነዉ? የሚለዉን በመፈተሽ ኘሮግራሞችን አስተካክለናል ማለታቸዉ ይታወሳል።
ዩንቨርስቲዉ በሽግግር ሂደቱ ለጊዜዉ ተማሪዎች እንዳይቀበል በማቆየት የአካዳሚክ ኘሮግራሞች ግምገማን ማዋሀድ እና የማጣመር እርምጃዎችን ማድረጉን ተሰጥቶ በነበረዉ መግለጫ ተነስቶ ነበር።
ቁምነገር አየለ
መጋቢት 08/2018 ዓ.ም
