ወንጀለኛ ተጨዋች ያስፈረመው ክለብ ተቀጣ

ኮከብ ተጫዋቹ በነፍስ ግድያ ሙከራ እና በዕፅ ዝውውር ወንጀል የተከሰሰበት ክለብ 27 ነጥብ ተቀነሰበት።

የጀርመኑ ስፓቪጂ ሃይድሃውዘን (SpVgg Haidhausen) ክለብ በክልላዊ የሊጉ ውድድር ከአናትተቀምጦ የነበረ ሲሆን፣ ለዚህ ውጤቱም የመስመር አጥቂው ማቲዮ ቪድማር ዘጠኝ ጎሎች ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው።

ይህ የ34 ዓመት ጎልማሳ ከ2014 ጀምሮ ለበርካታ የአካባቢው ክለቦች በመጫወቱ በባቫሪያን እግር ኳስ ውስጥ በደንብ የሚታወቅ ስም ነበር። ነገር ግን ባለፈው ታህሳስ ወር ላይ አንድ ግለሰብ በሙኒክ ኦበርሴንድሊንግ (Obersendling) ሰፈር ቢ.ኤም.ደብሊው መኪናውን ወደ ፖሊሶች በመንዳት ለመግጨት ከሞከረ በኋላ የታጠቁ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር አውለውታል።

በግለሰቡ መኖሪያ ቤት ውስጥ አምስት ኪሎ የሚመዝን ክሪስታል ሜዝ (Crystal Meth) እና ሄሮይን የተባሉ እፆች፣ እንዲሁም የጦር መሳሪያዎች፣ ሀሰተኛ ፓስፖርቶች እና 50,000 ዩሮ (43,000 ፓውንድ) ጥሬ ገንዘብ መገኘቱ ተዘግቧል። መርማሪዎች ግለሰቡ “ማቲዮ ቪድማር” የሚል ሀሰተኛ ማንነት በመጠቀም በእግር ኳስ ተጫዋችነት ሲንቀሳቀስ እንደነበረ ደርሰውበታል።

እሱ በአሁኑ ጊዜ በቁጥጥር ስር የሚገኝ ሲሆን፣ በነፍስ ግድያ ሙከራ፣ በጦር መሳሪያ ይዞታ እና በዕፅ ዝውውር ወንጀሎች ክስ ተመስርቶበታል።

የባቫሪያ እግር ኳስ ማህበር (BFV) ደግሞ፣ ክለቡ በሀሰተኛ ስም የተመዘገበ ተጫዋችን በማሰለፉ ምክንያት 27 ነጥብ እንዲቀነስበት ወስኗል። ይህም ክለቡ ወደ ቀጣዩ ሊግ ለማደግ የነበረውን ተስፋ አጨልሞታል።

ይሁን እንጂ ክለቡ ስለ ቪድማር ድርብ ማንነት የሚያውቀው ነገር እንዳልነበረ በመግለጽ ይግባኝ ጠይቋል። የክለቡ ሊቀመንበር ጁሴፔ ሺያልዶን (Giuseppe Scialdone) ሲናገሩ “ይህ እብደት ነው። እሱ ማንነቱ የማይታወቅ ተራ ሰው ነበር ማለት ነው” ብለዋል።

“የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ስቱዲዮ (fitness studio) እንዳለው ይናገር ነበር። የምዝገባ ቅጹን ሞልቷል፤ ታዲያ ትክክለኛ አለመሆኑን እንዴት ማረጋገጥ እንችል ነበር? እሱን ወደ ክለባችን ለማምጣት የዝውውር ሂሳብ ጭምር ሁሉ ከፍለናል፤ እኛ በደለኛ አይደለንም፣ እንዲያውም እኛሰለባዎች ነን። ሁላችንም የአጭበርባሪ ሰለባ ሆነናል፤ የባቫሪያ እግር ኳስ ማህበር (BFV) ውሳኔ ፍትህ እንደሚያመጣልን ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉም አክለዋል።

ምስጋናው ታደሰ

መጋቢት 8/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *