ዋሽንግተን እና ቴህራን ግጭቱን እንደሚያባብሱ ካስጠነቀቁ በኋላ፣ የኢራን ጦርነት አራተኛ ሳምንቱን ሲይዝ ሰኞ ዕለት በእስያ የሚገኙ ዋና ዋና የአክሲዮን ገበያዎች በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሰዋል። የጃፓኑ መመዘኛ ኢንዴክስ ወደ 3.6በመቶ ዝቅ ብሎ የዋለ ሲሆን፣ የደቡብ ኮሪያው ኮስፒ ደግሞ ወደ 6 በመቶ ወደሚጠጋ መጠን ቀንሷል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት በሰጡት ማስጠንቀቂያ፣ ኢራን ቁልፍ የሆነውን የሆርሙዝ የባህር መስመር ካልከፈተች የሀገሪቱን የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች “እንደሚያወድሙ” ገልጸዋል። ኢራን በበኩሏ ለማንኛውም እንዲህ ዓይነት ጥቃት ምላሽ የምትሰጠው በክልሉ ያሉ ቁልፍ መሰረተ ልማቶችን፣ የኃይል ተቋማትን ጨምሮ ኢላማ በማድረግ እንደሆነ አስታውቃለች።
ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ አብዛኛውን ጊዜ በዚሁ የባህር መስመር የሚያልፉትን ዘይትና ጋዝ በእጅጉ የሚደገፉ በመሆናቸው በዚህ ግጭት ክፉኛ ተጎድተዋል።
አሜሪካ እና እስራኤል በየካቲት 28 ቀን በኢራን ላይ ጥቃት ከሰነዘሩበት ጊዜ ጀምሮ፣ ኢራን የዓለማችን እጅግ ስራ የሚበዛበትን የዘይት ማጓጓዣ መስመር የሆርሙዝ የባህር ሰርጥን እንቅስቃሴ ግታለች። በዓለም ላይ ካለው የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ምርት ውስጥ 20 በመቶ የሚሆነው በዚህ የውሃ መስመር የሚያልፍ በመሆኑ፣ ጦርነቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ እንዲንር አድርጓል።
ሰኞ ዕለት የዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ ኃላፊ ፋቲህ ቢሮል እንደተናገሩት፣ ይህ ጦርነት ዓለም ላለፉት አሥርተ ዓመታት ካጋጠሟት እጅግ የከፋ የኢነርጂ ቀውስ ጋር እንድትጋፈጥ ሊያደርጋት ይችላል።
በአውስትራሊያ ዋና ከተማ በሚገኘው ብሔራዊ የፕሬስ ክለብ ንግግር ያደረጉት ቢሮል፣ አሁኑን ቀውስ እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ ከነበረው እና ሩሲያ በ2022 ዩክሬንን በመውረሯ ምክንያት ከተከሰተው ቀውስ ጋር አነጻጽረውታል።
“ይህ ቀውስ ባለንበት ሁኔታ፣ ሁለት የነዳጅ ቀውሶች እና አንድ የጋዝ ክሽፈት በአንድ ላይ ተደምረው የመጡ ይመስላል” ሲሉ ተናግረዋል።
ሀና ሰይፉ
መጋቢት 14/2018 ዓ.ም
