የኢራን መንግስታዊ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት፥የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ቴህራን በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ጦርነት ለማቆም ስምምነት ትፈልጋለች” ካሉ ከአንድ ቀን በኋላ የኢራን ወታደራዊ ቃል አቀባይ አሜሪካ ከራሷ ጋር እየተደራደረች መሆኑን ገልጸዋል።
ዋሽንግተን ግጭቱን ለማስቆም ያለመ ባለ 15 ነጥብ እቅድ አርቅቃ በፓኪስታን በኩል ለቴህራን መላኳን ጉዳዩን የሚያውቁ አንድ ግለሰብ ለሮይተርስ ተናግረዋል።
የኢራን የታጠቁ ኃይሎች የተባበሩት ዕዝ ቃል አቀባይ ኢብራሂም ዞልፋቃሪ፥በአሜሪካን አመራር ሲያፌዙ የውስጥ ትግላችሁ ደረጃ ከራሳችሁ ጋር እስከመደራደር ደርሷል ብለዋል።
እንደ እኛ ያሉ ሰዎች እንደ እናንተ ካሉ ሰዎች ጋር መቼም ሊስማሙ አይችሉም ብለዋል።
ዞልፋቃሪ አክለውም፥ ዋሽንግተን የቀጣናው መረጋጋት በኢራን የታጠቁ ኃይሎች እንደሚረጋገጥ እስካልተቀበለች ድረስ የአሜሪካ ኢንቨስትመንቶች እና ከጦርነቱ በፊት የነበሩ የነዳጅ ዋጋዎች ሊመለሱ እንደማይችሉ ገልጸዋል።
ሳራ ዮሐንስ
መጋቢት 16/2018 ዓ.ም
