የተባበሩት መንግሥታት የፍልሰት ድርጅት 2025 በቀይ ባሕር የስደተኞች መስመር ላይ እጅግ አስከፊው ዓመት እንደነበር ገለጸ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደገለጸው፤ 2025 ከአፍሪካ ቀንድ ወደ ዓረብ ባሕረ ሰላጤ በሚያመራው ‹‹ምሥራቃዊ መስመር››ተብሎ በሚጠራው የስደተኞች መንገድ ላይ ከፍተኛ የሞት ቁጥር የተመዘገበበት ዓመት ሆኗል።

አብዛኞቹ ተጎጂዎች ከኢትዮጵያ የመጡ መሆናቸውን ድርጅቱ ገልጿል።

ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (IOM) በዚህ የቀይ ባሕር የባሕር ላይ ጉዞ የሞቱ ወይም የጠፉ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ በመጨመር 9መቶ22 መድረሱን አስታውቋል።

በየዓመቱ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ከኢትዮጵያ፣ ከሶማሊያ እና ከአጎራባች አገሮች የመጡ ስደተኞች በአብዛኛው ከጅቡቲ ወደ የመን የባህር ላይ ጉዞ ያደርጋሉ፡፡

እነዚህ ስደተኞች ወደ ሀብታም የባሕረ ሰላጤ አገሮች የሚጓዙት የቀን ሠራተኛ ወይም የቤት ሠራተኛ ሆኖ ለመሥራት በማሰብ ነው።

ይሁን እንጂ ብዙዎቹ በዓረብ ባሕረ ሰላጤ ደሃ በሆነችውና ላለፉት አሥር ዓመታት ገደማ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በምትገኘዉ የመን ውስጥ ይገኛሉ። አንዳንዶቹ ስደተኞች እዚያ ባለው አስጊ ሁኔታ ምክንያት ወደ አገራቸው ለመመለስ መርጠዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተጨማሪ አደጋዎችን ለመከላከል ሲባል አስተማማኝ የፍልሰት መስመርን ለማበረታታት ከጅቡቲ መንግሥት ጋር እየሠራ መሆኑን ገልጿል።

ድርጅቱ በ2025 በአደገኛ የስደተኞች መስመሮች ላይ በአጠቃላይ ወደ 8 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች መሞታቸውን ወይም መጥፋታቸውን ባለፈዉ ወር አስታውቆ ነበር።

ይህ በቀን በአማካይ የ21 ሰዎች ሞትን የሚያሳይ ቢሆንም፤ የገንዘብ ድጋፍ መቀነስ በሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እና የሟቾችን ቁጥር በመከታተል ረገድ ተጽዕኖ ስለፈጠረ ትክክለኛው የሟቾች ቁጥር ከዚህም በእጅጉ ሊበልጥ እንደሚችል ድርጅቱ አመልክቷል።

እስከዳር ግርማ

መጋቢት 17/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *