በፍርድ ቤቶች የለዉጥ ፍኖተ ካርታ በትኩረት እንዲሰራበት ይደረጋል የተባለዉ ይህ የፍርድ ቤት መር የአስማሚነት ስርዓት የተከራካሪዮች መዝገብ በስምምነት እንዲቋጭ የማድረግ ሂደት ቢኖረም ዉጤታማ መሆን ላይ ግን ጥያቄ አስነስቷል።
የፌደራል ፍርድ ቤቶችን የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያደመጠው የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክንያቶቹን ጠይቋል።
በሪፖርቱ በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች እንዲቋጩ ተደርገዋል ከተባሉ መዛግብት 14 በመቶ አፈፃፀም ያሳዩ፣በከፍተኛ ፍርድ ቤት 3.7 በመቶ እንዲሁም በፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ከቀረቡ 54 በመቶ መዛግብት ሁለቱ ተከራካሪ ወገኖች ባለመቅረባቸው እንዳልተሳኩ ተገልጿል።
ለቋሚ ኮሚቴዉ የችግሩን ምክንያቶች ያስረዱት የፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤቶች ፕሬዝዳንት ፉአድ ከድር በዚህ ስርዓት ሁለት ችግሮች እየገጠማቸው እንደሆነ ገልፀዋል።
የግራ እና ቀኝ ተከራካሪዎች መዝገቦቹን በክርክር የመጨረስ ፍላጎት እክል እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።
የባለጉዳዮች ተከራካሪ ጠበቆች የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ስርአት ላይ ችግር መፍጠራቸዉን አስረድተዋል።
ማሳያ ብለዉ ካነሷቸዉ ምክንያቶች አንዱም ለአስማሚ የተቀጠሩ ዕለት አለመምጣት ሲሆን፤ ለአስማሚ ቀጠሮ አለመምጣት ቅጣት የሚቀጣበት መመሪያ ቢኖርም ቀርተዉ ቅጣቱን እየከፈሉ እንደሆነ አንስተዋል።
ከዚህ ሌላ የፍርድ ቤቶቹ የአስማሚ ባለሙያዎች ብቃት አናሳ መሆን እና የሙያ እዉቀታቸዉ ዉስን መሆን የዉስጥ ችግር መሆኑን ጠቅሰዋል።
የቋሚ ኮሚቴዉ ዋና ሰብሳቢ ወ/ሮ እፀገነት መንግስቱ ለምን ተፈላጊ አልሆነም የሚለዉን መለየት ያስፈልጋል ብለዋል።
አያይዘዉም ተከራካሪዎች ሊያገኙት ያሰቡት ያልተገባ ጥቅም በምክንያትነት አንስተዋል ፤ይህንን የማይፈቅድ መመሪያ እንዲዘጋጅም አሳስበዋል።
ቁምነገር አየለ
ሚያዚያ 16/2018 ዓ.ም
