ፓኪስታን በአሜሪካ ጦር ተይዘው የነበረ የአንድ የኢራን መርከብ 22 አባላትን ዛሬ ሰኞ ለቴህራን እንደምታስረክብ አረጋግጣለች።
የእስላማባድ ባለስልጣናት ይህንን ውሳኔ “የመተማመን መገንቢያ እርምጃ” ሲሉ የገለጹት ሲሆን፤ ይህም በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ አካባቢ ያለውን ከፍተኛ ውጥረት ለማርገብ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
መርከበኞቹ በአሜሪካ የባህር ኃይል ቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በፓኪስታን በኩል አልፈው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ይህ የፓኪስታን እርምጃ በቅርቡ በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ላይ በተፈጠረው ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ፍጥጫ ሳቢያ በኢራን እና በምዕራባውያን ሀገራት መካከል የሻከረውን ግንኙነት ለማለስለስ የሚረዳ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ተደርጎ ተወስዷል።
ርክክቡ ዛሬ ሰኞ እለት እንደሚከናወን የሚጠበቅ ሲሆን፤ እስላማባድ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ያላትን ፍላጎት የምታሳይበት እንደሆነም አስታውቃለች መባሉን የዘገበው አናዶሉ ነው።
ልዑል ወልዴ
ሚያዚያ 26/2018 ዓ.ም
