የሞሳድ ዳይሬክተር ቀጠናዊ ጥረቶችን ለማስተባበር ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በተደጋጋሚ መጓዛቸው ተሰማ

የእስራኤል የውጭ ደህንነት መስሪያ ቤት ወይም የሞሳድ ዳይሬክተር ዴቪድ ባርኒያ፣ በኢራን ላይ የሚከናወኑ ኦፕሬሽኖችን እና ቀጠናዊ ጥረቶችን ለማስተባበር ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በተደጋጋሚ መጓዛቸውን አንድ አዲስ ዘገባ አመላከተ።

እንደ መረጃው ከሆነ፣ ዳይሬክተሩ ዴቪድ ባርኒያ እነዚህን ሚስጥራዊ ጉብኝቶች ያደረጉት እስራኤል በኢራን ላይ የምታከናውናቸውን ዘመቻዎች ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግና ከአካባቢው አጋር አገራት ጋር የደህንነት ትብብርን ለማጠናከር በማለም ነው።

ባርኒያ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከከፍተኛ የደህንነት ኃላፊዎች ጋር ተገናኝተው መክረዋል የተባለ ሲሆን፣ ውይይቶቹም በዋናነት የኢራንን ቀጠናዊ ተጽዕኖ መገደብ እና የደህንነት ስጋቶችን በጋራ መከላከል በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ያተኮሩ ናቸው።

ይህ መረጃ ይፋ የሆነው እስራኤል እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የአብርሃም ስምምነትን ተከትሎ ግንኙነታቸውን ካጠናከሩ በኋላ ነው።

በደህንነት እና በወታደራዊ ዘርፍ ያላቸው ትብብር እያደገ መምጣቱም ተዘግቧል።

እስካሁን ድረስ ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስም ሆነ ከእስራኤል በኩል ስለ ጉብኝቶቹ በይፋ የተሰጠ መግለጫ የለም።

ይሁን እንጂ የባርኒያ ጉዞዎች እስራኤል ከዓረብ አገራት ጋር በመሆን በኢራን ላይ የጋራ ግንባር ለመፍጠር የምታደርገውን ጥረት ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል ሲል ጄሩሳሌም ፖስት ዘግቧል።

ልዑል ወልዴ

ግንቦት 05/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *