በአዲስ አበባ ህገ-ወጥ አሰራር በተገኘባቸው ከ350 በላይ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የሸማቾች መብት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ባለፉት አስር ወራት የከተማዋን ሸማቾች መብት ከማስጠበቅ አንጻር ያከናወናቸው ተግባራት አመርቂ መሆናቸውን ገለጸ።

የዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር አቶ መሀመድ አላቦ  እንደገለጹት፤ ዳይሬክቶሬቱ ባለፉት አስር ወራት ሸማቾች በተደራጀ አግባብ መብቶቻቸውን ማስከበር እንዲችሉ ሰፊ የድጋፍ ስራዎችን አከናውኗል።

ከሸማቾች በደረሱ ጥቆማዎች መሠረትም ጥራታቸውን ያልጠበቁ፣ ለፀሐይና ለብልሽት የተጋለጡ፣ ከደረጃ በታች የሆኑ እንዲሁም የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ምርቶች፣ ምግቦችና መጠጦች ከገበያ እንዲወገዱ መደረጉን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

ቢሮው በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሠረት በ8588 ነፃ የስልክ መስመር በደረሱ ጥቆማዎች መነሻነት እርምጃዎችን መውሰዱን ያመለከቱት አቶ መሀመድ፤ በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ላይ ሲንቀሳቀሱ በነበሩ 40 ነጋዴዎች ላይ ከገበያ ትስስር የመውጣት፣ በ139 ነጋዴዎች ላይ የመጨረሻ ደረጃ ማስጠንቀቂያ እንዲሁም በ179 ነጋዴዎች ላይ የመጀመሪያ ደረጃ ማስጠንቀቂያ የመስጠት እርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ባለፉት አስር ወራት 351 ቅሬታዎች በስልክ፣ 296 ቅሬታዎች ደግሞ በአካል ቀርበው ተገቢው ምላሽ እንዲያገኙ ተደርጓል።

ዳይሬክቶሬቱ አሳሳች ማስታወቂያዎችን እና የሸማቾችን መብት የሚጎዱ ተግባራትን ለመከላከል የጀመረውን ቁጥጥር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ መሀመድ አላቦ ጨምረው ገልጸዋል።

አቤል እስጢፋኖስ

ግንቦት 10/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *