የዩኤስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጦርነቱን ለማቆም የሚደረገው ድርድር በመስተጓጎሉ ለኢራን “ጊዜው እየረፈደ ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል (Truth Social) ገጻቸው ላይ “በፍጥነት መንቀሳቀስ ይሻላቸዋል፤ ካልሆነ ግን ምንም ነገር አይተርፍላቸውም፤ ጊዜው አሁን ነው!” ሲሉ ጽፈዋል።
የእስራኤሉ ታይምስ ኦፍ እስራኤል የኔታንያሁ ቢሮን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ይህ መልዕክት የተላለፈው ፕሬዝዳንቱ እሁድ ዕለት ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ነው፤በሌላ በኩል የኢራን መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት፤ ዩኤስ ጦርነቱን ለማቆም ቴህራን ላቀረበችው የቅርብ ጊዜ የውሳኔ ሃሳብ በሰጠችው ምላሽ ላይ ምንም አይነት ተጨባጭ ቅናሽ አላደረገችም።
ከዋሽንግተን ወገን የአቋም መለስለስ አለመኖሩ “በድርድሩ ላይ መጉዋተትን ” ያስከትላል ሲል መህር (Mehr) ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡
ይህ የአሁኑ የ ትራምፕ ዛቻ በፈረንጆቹ ሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከመታወጁ ጥቂት ቀደም ብሎ፣ ኢራን ጦርነቱን ለማቆም ካልተስማማች “አንድ ሙሉ ስልጣኔ” ይጠፋል ሲሉ ካስተላለፉት ማስፈራሪያ ጋር የሚመሳሰል ነው፤ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ የቴህራንን ጥያቄዎች “ፈጽሞ ተቀባይነት የሌላቸው” በማለት ውድቅ ካደረጉ በኋላ የተኩስ አቁሙ “አስጊ ሁኔታ” ላይ እንደሚገኝ አስጠንቅቀው ነበር።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኢል ባጋኢ በበኩላቸው ጥያቄዎቹ “ኃላፊነት የተሞላባቸው” እና “ለጋስ” መሆናቸውን ጠቅሰው ተከራክረዋል ፤ የኢራን ከፊል-መንግስታዊው የታስኒም (Tasnim) ዜና አገልግሎት እንደገለጸው፣ ጥያቄዎቹ በሁሉም ግንባሮች ላይ ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆም ፤ ዩኤስ በኢራን ወደቦች ላይ የጣለችው የባህር ኃይል እገዳ እንዲነሳ እና በኢራን ላይ ተጨማሪ ጥቃቶች እንዳይፈጸሙ ዋስትና መስጠትን ያካትታሉ በተጨማሪም ለጦርነት ውድመት ካሳ እንዲከፈል የሚጠይቅ እና ኢራን በሆርሙዝ የባህር ሰርጥ ላይ ያላትን ሉዓላዊነት የሚያጎላ ጥያቄ ማካተታቸው ተነግሯል።
የኢራን ከፊል-መንግስታዊው የፋርስ (Fars) ዜና አገልግሎት እሁድ ዕለት እንደዘገበው ዋሽንግተን ለቴህራን የውሳኔ ሃሳብ ምላሽ አምስት ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጣለች፤ከቅድመ ሁኔታዎቹ መካከል ኢራን አንድ የኑክሌር ጣቢያ ብቻ በሥራ ላይ እንድታቆይ እና በከፍተኛ ደረጃ የበለፀገውን ዩራኒየም ክምችቷን ለዩኤስ እንድታስረክብ የሚጠይቅ ይገኝበታል።
ትራምፕ አርብ ዕለት እንደጠቆሙት፣ ኢራን የኑክሌር ፕሮግራሟን ለ20 ዓመታት እንድታቋርጥ የቀረበውን ሃሳብ ሊትቀበል እንደምትችል ገልጸዋል ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ዋነኛው የውዝግብ ነጥብ የነበረ ሲሆን፤ ፕሮግራሙ ሙሉ በሙሉ እንዲቆም ከነበራቸው ጥያቄ ወደኋላ የማፈግፈግ ለውጥ ማሳያ ይመስላል።
ሀና ሰይፉ
ግንቦት 10/2018 ዓ.ም
