ከትንባሆ ጭስ ነፃ ከባቢን ለመፍጠር በተከናወኑ ተግባራት የምግብ ተቋማትና ካፌዎች በተጨባጭ የጤና ተቋማት ደግሞ የተሟላ በሚባል ደረጃ ነፃ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን አስታውቋል።
ተቋሙ በዘርፋ ያከናወናቸው የቁጥጥርና የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች ውጤት ማምጣታቸው በገለልተኛ አካል በተደረገ ጥናት መረጋገጡን አመልክቷል።
በዚህም በመዲናዋ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት 79 በመቶ የሚሆኑ ተቋማት ከትንባሆ ጭስ ነፃ መሆናቸው መረጋገጡን ገልጿል።
ከቁጥጥር ስራዎቹ ትይዩ የአዲስአበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ትምባሆን ከአዋኪ ድርጊቶች ዝርዝር ውስጥ በማካተት ከማህበራዊ ተቋማት እስከ 500 ሜትር ባለው ርቀት ላይ እንዳይጨስ ክልከላ ማስቀመጡም ተጠቁሟል።
በተጨማሪም እንደ አዲስ በለሙ የኮሪደር ቦታዎች ማጨስን የሚከለክሉ ምልክቶች መተከላቸውንና የሲጋራ ቁራጭ መጣል 2000 ብር እንደሚያስቀጣ ባለስልጣኑ ጠቅሷል።
ሆኖም የምሽት መዝናኛ ቤቶች መስፋፋት ከቁጥጥር ስራው በቂ አለመሆን ጋር ተዳምሮ ተግዳሮት ሆኖ መቀጠሉ ተነስቷል።
ሐመረ ፍሬው
ግንቦት 11/2018 ዓ.ም
