በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት አስተዳደር ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ገበየሁ ሊካሳ እንደገለጹት፤ ተቋሙ የመጪውን ክረምት ታሳቢ በማድረግ በመላ ሀገሪቱ ሰፋፊ የቅድመ መከላከል ጥገናዎችን እያከናወነ ይገኛል።
በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ62 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የመካከለኛ ቮልቴጅ መስመሮች ፈተሻ ተደርጎባቸዋል ብለዋል።
በፍተሻው ከተለዩት ችግሮች መካከልም 92 በመቶ የሚሆኑት የመስመር ችግሮች እና 86 በመቶ የሚሆኑት የትራንስፎርመር ብልሽቶች ጥገና ተደርጎላቸዋል በማለት ገልጸዋል።
ስራው በተለይ የዛፍ ቅርንጫፎችን ማጽዳት፣ ያረጁ ምሰሶዎችን መቀየር እና የረገቡ ሽቦዎችን መወጠር ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ አዲስ አበባ ላይ የኤሌክትሪክ መቆራረጥን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መጠናቀቂያ ላይ ደርሰዋል ተብሏል፡፡
በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ያሉ 50 ኪሎ ሜትር ከተሞችን የሚያካትተው የ”አትድራፕ” (ATDRAP) ፕሮጀክት አፈጻጸም 97.6 በመቶ ደርሷል ሲሉ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት አስተዳደር ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ገበየሁ ሊካሳ አሳውቀዋል።
ይህ ፕሮጀክት 10 አዳዲስ ሰብስቴሽኖችን መገንባትና 642 ኪሎ ሜትር መስመር መልሶ መገንባትን ያካተተ መሆኑ ተነግሯል።
አዲስአለም አበበ
ሰኔ 02/2018 ዓ.ም
