የሀገሪቱን የወጪና ገቢ ንግድ ሥርዓት ለማዘመን፣ ሕጋዊ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታትና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየረቀቀ የመጣውን የኮንትሮባንድ ወንጀል ለመከላከል ታስቦ የተዘጋጀው አዲሱ የጉምሩክ አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ መጽደቁ ይታወሳል።
ጣቢያችን “የጉምሩክ አዋጅ ማሻሻያ ” በሚለው ሰነድ ላይ የተመለከተው ረቂቅ አዋጅ፣ በሥራ ላይ ባለው ሕግ ላይ የታዩ አሠራርን የሚያዘገዩ ክፍተቶችን በከፍተኛ ደረጃ የሚቀይር ነው።
በዚህ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ ትልቅ ትኩረት ካረፉባቸው ጉዳዮች መካከል የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል የወጣው ጠንካራ ድንጋጌ አንዱ ነው።
ቀደም ሲል በአዋጅ ቁጥር 1160/2011 ተሻሽሎ የነበረው ሕግ፣ የኮንትሮባንድ ዕቃ የጫነ ተሽከርካሪ ባለቤት ወንጀሉ ላይ በቀጥታ ካልተሳተፈ ንብረቱ ሳይወረስ የ100 ሺህ ብር ቅጣት ብቻ እንዲጣልበት ይደነግግ ነበር።
ይሁን እንጂ ይህ አሠራር ኮንትሮባንዲስቶች ገንዘቡን እየከፈሉ ሕገ-ወጥ ንግዱ ይበልጥ እንዲጧጧፍ በር የከፈተ መሆኑ በሰነዱ ላይ ተመልክቷል።
አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ይህንን ችግር ለመቅረፍ፣ ዕቃዎችን ለመደበቅ የሚያስችል አካል ተገጥሞለት የተገኘ ወይም ሙሉ በሙሉ የኮንትሮባንድ ዕቃ ጭኖ የተገኘ ማጓጓዣ/ተሽከርካሪ፣ የዕቃው ግምታዊ ዋጋ ከግምት ውስጥ ሳይገባ ተወርሶ ለመንግሥት ገቢ እንዲሆን ይደነግጋል።
ይሁን እንጂ ማጓጓዣው ከመወረሱ በፊት ባለቤቱ ማስረጃ የመከላከል ዕድል እንዲሰጠው ሥርዓት ተዘርግቷል።
ከዚህም በተጨማሪ ከሕገ-ወጥ ዕቃዎች ሽያጭ የሚገኘው ገቢ የጉምሩክ ኮሚሽንን የመከላከያና የሎጂስቲክስ አቅም ለመገንባት (ለአቅም ግንባታ) እንዲውል ይደረጋል።
በሌላ በኩል፣ በአስመጪዎችና በነጋዴዎች ላይ ይደርስ የነበረውን ፍትሃዊ ያልሆነ አሠራር ለማስቀረት ትልቅ ማሻሻያ ተደርጓል።
በሥራ ላይ ባለው አዋጅ መሠረት አንድ አስመጪ በጉምሩክ ኮሚሽን በተጣለበት ቀረጥና ታክስ ቅር ተሰኝቶ ለታክስ ይግባኝ ኮሚሽን አቤቱታ ማቅረብ የሚችለው የተጠየቀውን ገንዘብ 100 በመቶ ሙሉ በሙሉ ከፈለ በኋላ ብቻ ነበር።
ይህ አሠራር የዜጎችን አቤቱታ የማቅረብ መብት የሚገድብና አስመጪዎች ከረጅም ክርክር በኋላ ገንዘቡ እንዲመለስላቸው ሲወሰን እንኳ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ ፍትሃዊ እንዳልነበር ተገልጿል።
አዲሱ ረቂቅ ሕግ አስመጪው ያመነበትን ቀረጥ ከፍሎ፣ ክርክር ያስነሳውን የቀረጥና ታክስ መጠን 50 በመቶ (ግማሹን) ብቻ በማስያዝ ይግባኝ ማቅረብ እንዲችል ፈቅዷል።
ከእነዚህ ዋና ዋና ነጥቦች በተጨማሪ ረቂቅ አዋጁ የሚከተሉትን ወሳኝ የለውጥ ማሻሻያዎች አካቷል፦
ዕቃዎችን በክፍልፋይ መልቀቅ፦ አስመጪዎች በገንዘብ እጥረት ምክንያት ሁሉንም ቀረጥ በአንድ ጊዜ መክፈል ካልቻሉ፣ ለሚለቀቀው ዕቃ ልክ ቀረጥ እየከፈሉ ዕቃቸውን በከፊል (በክፍልፋይ) ማውጣት እንዲችሉ ተፈቅዷል።
የመጋዘን ቆይታ ጊዜ ማሻሻል፦ የጉምሩክ ፎርማሊቲዎችን ለማጠናቀቅ ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘበ የጊዜ ማሻሻያ ተደርጓል። በዚህም መሠረት በባሕርና በየብስ የመጡ ዕቃዎች መጋዘን ውስጥ የሚቆዩበት ጊዜ ወደ 45 ቀናት፣ በአየር የመጡት ደግሞ ወደ 30 ቀናት ከፍ እንዲል ተደርጓል።
የገንዘብ ምንዛሪ ተመን አቆጣጠር፦ ለቀረጥ ስሌት የሚሆን የምንዛሬ ተመን የሚወሰደው ዲክላራሲዮኑ ለኮሚሽኑ ቀርቦ ተቀባይነት ባገኘበት ቀን በብሔራዊ ባንክ በሚገለጸው ጠቋሚ የምንዛሬ ልክ እንዲሆን ተወስኗል። ይህም መንግሥት ያጣ የነበረውን ከፍተኛ ታክስ ያስመግባል ተብሏል።
የታማኝ ነጋዴዎች ልዩ መብት፦ቀደም ሲል ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ብቻ ይሰጥ የነበረው “በደብዳቤ ዋስትና” ዕቃ የመልቀቅ መብት፣ አሁን ታማኝ ግብር ከፋዮችን ለማበረታታት ልዩ መብት ለተፈቀደላቸው የኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች (AEO) ጭምር እንዲፈቀድ ረቂቁ ይደነግጋል።
ይህ የጉምሩክ አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ የጸና እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን፣ አጠቃላይ የጉምሩክ አሠራሩን ሙሉ በሙሉ ለማደስ የሚያስችል ጥናት በቅርቡ እንደሚጀመርም ታውቋል።
ለዓለም አሰፋ
ሰኔ 03/2018 ዓ.ም
