የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት የእርስ በእርስ የቁጥጥር ስርዓት ይበልጥ ማጠናከሩን አስታወቀ

​የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት የመገናኛ ብዙሃንን የእርስ በእርስ የቁጥጥር ስርዓት ይበልጥ ማጠናከሩን እና ይህም ሙያዊ የስነ-ምግባር ጥሰቶች በምክር ቤቱ የግልገላ ዳኝነት አካል እንዲታዩ የተሻለ እድል መፍጠሩን አስታውቋል።

​ምክር ቤቱ ከጀርመን የልማት ትብብር (GIZ Ethiopia) ጋር በመተባበር ተደራሽነቱን ለማስፋት በርካታ ውጤታማ ስራዎችን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለትም የምክር ቤቱን ስራዎች ለማስተዋወቅ የሚያገለግሉ የመልቲ ሚዲያ ውጤቶች የርክክብ መርሃ-ግብር ተካሂዷል።

በጀርመን መንግስት የገንዘብ ድጋፍ የተከናወነው ይህ ፕሮጀክት የቅሬታ ማቅረቢያ ዘዴዎችን የማዘመን፣ ተቋማዊ ድረ-ገጽን በአዲስ መልክ የማደራጀት እና ህብረተሰቡ የሙያ ጥሰቶችን ሪፖርት የሚያደርግባቸውን አማራጮች የማስተዋወቅ ስራዎችን ያካተተ ነው።

​የምክር ቤቱ የግልገላ ዳኝነት አሰራርን ለህብረተሰቡ ለማስተዋወቅ በ32 የማህበረሰብ ሬዲዮ እና በ5 የማህበረሰብ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች በተለያዩ ቋንቋዎች የማስታወቂያ ዘመቻዎች የተከናወኑ ሲሆን፣ በዚህም ህብረተሰቡ የሚስተዋሉ የስነ-ምግባር ጥሰቶችን ለምክር ቤቱ ማመልከት መጀመሩ ተገልጿል።

በዚህ መሰረት ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በህዝብ፣ በንግድ፣ በህትመት እና በበይነ-መረብ ሚዲያዎች ላይ የታዩና ከጋዜጠኝነት ስነ-ምግባር ጥሰት ጋር የተገናኙ 25 ቅሬታዎች ለምክር ቤቱ የግልገላ ዳኝነት አካል ቀርበው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

አቤል እስጢፋኖስ

ሰኔ 04/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *