ደቡብ አፍሪካ በአንድ ሳምንት ውስጥ ከ2 ሺህ 7መቶ በላይ የውጭ ሀገር ዜጎችን ወደ ሀገራቸው መለሰች

ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በህገ-ወጥ ስደት ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እንደሚወስዱ ቃል ከገቡ በኋላ ባለው አንድ ሳምንት ውስጥ፤ደቡብ አፍሪካ 2 ሺህ 7መቶ45 የውጭ ሀገር ዜጎችን ወደ ሀገራቸው መመለሷን የሀገሪቱ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ገልጸዋል፡፡

ከአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚዎች አንዷ የሆነችው ደቡብ አፍሪካ፤ከመላው አህጉሪቱ በህጋዊም ሆነ በህገ-ወጥ መንገድ የሚመጡ ስደተኛ ሰራተኞችን ለረጅም ጊዜ ስትስብ ቆይታለች።

ሆኖም ከ30 በመቶ በላይ በሆነ ከፍተኛ የስራ አጥነት መጠን የተጠመደችው ሀገሪቱ በቅርብ ሳምንታት የተከሰቱ አዳዲስ ግጭቶችን ጨምሮ ተደጋጋሚ በስደተኞች ላይ ያነጣጠሩ ብጥብጦች አስተናግዳለች።

ዱላ፣ ጅራፍ እና ጋሻ የያዙ ደቡብ አፍሪካውያ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተዘዋወሩ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው የውጭ ሀገር ዜጎች እስከ ሰኔ 30 ድረስ ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ሲያስተላልፉ ሰንብተዋል።

ንግዶች በመዘረፋቸው እና የውጭ ዜጎች ዒላማ በመደረጋቸው ምክንያት እየጨመረ የመጣው የደህንነት ስጋት የናይጄሪያ፣ ማላዊ፣ ጋና፣ ዚምባብዌ እና ሞዛምቢክ ዜጎች በመንግስታቶቻቸው አማካኝነት የተዘጋጀውን በፍቃደኝነት ወደ ሀገር የመመለስ ጥሪ እንዲቀበሉ አድርጓቸዋል።

መንግስት እንደገለጸው ወደ ሀገራቸው ከተመለሱት መካከል አብዛኞቹ በሀገሪቱ ውስጥ በህገ-ወጥ መንገድ ይኖሩ የነበሩ ናቸው።

መንግስት እሁድ ዕለት እንደገለጸው የስደተኛ መጠለያ ካምፖችን የማያስተዳድር ሲሆን፤ በጊዜያዊነትም ቢሆን የማቋቋም ዕቅድ የለውም።

እንደ ሀገሪቱ የስታስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ ከሆነ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ከሦስት ሚሊየን በላይ የውጭ ሀገር ዜጎች ይኖራሉ፤ ይህም ከጠቅላላው የህዝብ ብዛት 5.1 በመቶ ያህሉ ነው።

እስከዳር ግርማ

ሰኔ 08/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *