በዩክሬን በተሰነዘሩት የሩሲያ ጥቃቶች የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፤ በታዋቂው የኪቭ ካቴድራል ላይ የእሳት አደጋ ተከሰተ

የሩሲያ ጦር በተለያዩ ዋና ዋና ከተሞች ላይ በሰነዘረው ተከታታይ ጥቃት በዩክሬን ቢያንስ የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት ማለፉን የክልሉ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

የኪቭ ወታደራዊ አስተዳደር ኃላፊ ቲሙር ትካቼንኮ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ‹‹በኪቭ አንድ ሕፃንን ጨምሮ 23 ሰዎች ቆስለዋል በሚያሳዝን ሁኔታም የሟቾች ቁጥር ወደ አራት አድጓል›› ብለዋል።

ቀደም ሲል የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኢጎር ክሊሜንኮ እንደገለጹት፤በሰሜን ምስራቅ ዩክሬን በምትገኘው ካርኪቭ ከተማ ‹‹የእሳት ማጥፋት ሥራ ላይ የነበሩ አምስት የሀገር ውስጥ ድንገተኛ አደጋ አገልግሎት አባላት ተገድለዋል።››

ክሊሜንኮ በቴሌግራም ገጻቸው ላይ ‹‹ቢያንስ ሌሎች 5 ሰዎች ቆስለዋል›› ሲሉ የጻፉ ሲሆን፤ ጉዳቱ የደረሰው ሩሲያ በድጋሚ በሰነዘረችው ጥቃት መሆኑን አንስተዋል።

የከተማዋ ከንቲባ ቪታሊ ክሊ ሰኞ ዕለት እንደተናገሩት በታዋቂው የኪቭ ፔቸርስክ ላቭራ የኦርቶዶክስ ገዳማት ግቢ ውስጥ የሚገኘው ዶርሚሽን ካቴድራል በሩሲያ ጥቃቶች ምክንያት የእሳት አደጋ ደርሶበታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሞስኮ በስተደቡብ 200 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኘው ቱላ በተባለችው የሩሲያ ከተማ ላይ የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላን በሰነዘረው ጥቃት ሦስት ሰዎች ሲገደሉ፤ ሌሎች ሦስት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የክልሉ ገዥ ሰኞ ዕለት አስታውቀዋል።

ዲሚትሪ ሚልዬቭ ‹‹ዛሬ ምሽት የቱላ ከተማ የመኖሪያ መንደር በሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ደርሶበታል›› ብለዋል፡፡

አክለውም ‹‹በጣም የሚያሳዝነው በደረሰን የመጀመሪያ ደረጃ መረጃ መሠረት ሦስት ሰዎች ተገድለዋል የአንድ ዓመት ሕፃንን ጨምሮ ሌሎች ሦስት ሰዎች ቆስለዋል›› ሲሉ ገልጸዋል።

ሀና ሰይፉ

ሰኔ 08/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *