የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ካስመዘገባቸው ከ5,000 በላይ ድርጅቶች ውስጥ የንብረት ምዝገባ ያደረጉት 631 ወይም (12%) ብቻ መሆናቸውን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የ2017 በጀት ዓመት የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ይፋ አደረገ።
የንብረት ምዝገባ ያደረጉት ጥቂት ድርጅቶችም ቢሆኑ መረጃቸው የተያዘው በሀርድ ኮፒ ብቻ በመሆኑ፣ ወደ አንድ ዲጂታል የመረጃ ቋት ስርዓት አለመግባቱ በቁጥጥር ስራው ላይ ከፍተኛ ክፍተት ፈጥሯል ሲል ገልጿል።
ዋና ኦዲተሩ በዚሁ ሪፖርት እንዳመለከተው፣ ባለስልጣን መ/ቤቱ ትክክለኛ አድራሻን አጣርቶ ባለመያዙ ምክንያት ድርጅቶቹን ለክትትል በሚፈልግበት ጊዜ በተሰጡት ስልክና አድራሻ ሊያገኛቸው አልቻለም ተብሏል።
ይህ ክፍተትም በአሁኑ ወቅት በርካታ ድርጅቶች የት እንደሚገኙ ለማወቅ አስቸጋሪ እንዳደረገው ሪፖርቱ አስታውቋል።
በተጨማሪም በርካታ ድርጅቶች ፈቃድ በሚወስዱበት ወቅት እንንቀሳቀሳለን ባሏቸው ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ውስጥ ምንም ዓይነት ስራ ሳይጀምሩ መቅረታቸው በኦዲቱ ተረጋግጧል።
ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጪ የበጎ አድራጎት ስራ የማይሰሩና ለገቢ ማመንጫ ብቻ የሚንቀሳቀሱ ተቋማት መኖራቸውን የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ ለዚህም የሳንፎርድ፣ ተርኪሽ ማሪፍ፣ ጀርመን እና ግሪክ ትምህርት ቤቶችን በማሳያነት ጠቅሷል።
እድላዊት ብርሃኑ
ሰኔ 16/2018 ዓ.ም
