እንደ አፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከል ማዕከል ኃላፊ ገለጻ፤ የኢቦላ ምርመራ ተደርጎላቸው ውጤታቸው ፖዘቲቭ የሆኑ ወደ 3መቶ የሚጠጉ ሰዎች ያሉበት አይታወቅም።
የታካሚዎቹ ያሉበት አለመታወቅ በክትትል ረገድ ክፍተቶች መኖራቸውን ያሳያል የተባለ ሲሆን፤ ገዳዩ ቫይረስ ያለ ምንም ቁጥጥር ሊሰራጭ ይችላል በሚል ከፍተኛ ስጋት እየፈጠረ ነው።
ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ወረርሽኙ ከግንቦት አጋማሽ ጀምሮ መከሰቱ ከታወጀ ወዲህ ከ1ሺህ1መቶ በላይ ሰዎች በኢቦላ መያዛቸውን አረጋግጣለች። ቢያንስ 2መቶ91 ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋል።
ወረርሽኙ በአብዛኛው በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብቻ የተገደበ ነው። ኡጋንዳ 20 ሰዎች መያዛቸውንና የሁለት ሰዎች ሞት ሪፖርት አድርጋለች።
ባለፈው ሳምንት ፈረንሳይ ከኮንጎ የተመለሱ አንድ ሐኪም የኢቦላ ምርመራ ውጤታቸው ፖዘቲቭ መሆኑን አስታውቃለች።
ነገር ግን የዓለም ጤና ድርጅት አዳዲስ ግምቶች እስከ መስከረም አጋማሽ ድረስ ከ8ሺህ በላይ ሰዎች ሊያዙ እና 1ሺህ4መቶ ሰዎች ሊሞቱ ይችላሉ ብሎ፤በሽታው ወደ ጎረቤት ሀገር ደቡብ ሱዳን የመሰራጨት እድሉ 70 በመቶ መሆኑን ትንበያ አድርጓል።
የኮንጎ ባለስልጣናት እና የጎረቤት ሀገራት የበሽታውን ስርጭት ለመቀነስ እየሰሩ መሆናቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ገልጾ፤ በከፋ ሁኔታ እስከ መስከረም ወር ድረስ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ60 ሺህ በላይ ሊደርስ ይችላል ብሏል።
አሁን ያለው ወረርሽኝ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተከሰተዉ ለ17ኛ ጊዜ ሲሆን፤ እስካሁን ከተመዘገቡት ሁሉ የከፋው ነው።
በምስራቅ ኮንጎ በቀጠለው ግጭት ምክንያት በወረርሽኙ በተጎዱ አካባቢዎች የሚገኙ ከአንድ ሚሊየን በላይ ሰዎች በጤና ባለሙያዎች ሊደረስባቸው አልተቻለም ተብሏል።
እስከዳር ግርማ
ሰኔ 22/2018 ዓ.ም
