ከእልቂት እና ከውድመት ጀርባ ሁልጊዜም ተስፋን የሚያለመልሙ ተአምራት አይጠፉም።
በቬንዙዌላ በደረሰው አስከፊ የመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ አገሪቱ በኃዘን ማቅ በለበሰችበት በዚህ ወቅት፣ መላውን ሕዝብ ያስለቀሰና ያስደሰተ አንድ አስገራሚ ክስተት ተመዝግቧል።
የመሬት መንቀጥቀጡ ከተከሰተ በትክክል ስድስት ቀናት አልፈዋል። ፍርስራሽ ውስጥ የተቀበሩ ሰዎችን በሕይወት የማግኘት ተስፋ ሙሉ በሙሉ እየተሟጠጠ በሄደበት በዚያ አስጨናቂ ሰዓት፣ አንድ የሦስት ዓመት ታዳጊ ሕፃን ከግዙፍ ፍርስራሾች ሥር በሕይወት ተገኝቷል። ይህንን ሕፃን ፈልጎ ተጫነው ኮንክሪት ውስጥ በሕይወት ሊያወጣው የቻለው የጆርዳን የነፍስ አድን ቡድን ነው።
ሕፃኑ ክሌይበር የተገኘው በላ ጉዋይራ ግዛት ውስጥ ከወደመ ሕንፃ ፍርስራሽ ሥር ሲሆን፣ የሀገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ዴልሲ ሮድሪጌዝ ይህንን ተአምራዊ አጋጣሚ ሲገልጹ “ይህ ሕፃን ለሕዝባችን ትልቅ የብርታትና የተስፋ ምንጭ ነው” ብለዋል።
የሕክምና እና የነፍስ አድን ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፣ አንድ ሰው በመሬት መንቀጥቀጥ ፍርስራሽ ውስጥ ከተቀበረ ከመጀመሪያዎቹ ሦስት ቀናት (72 ሰዓታት) በኋላ በሕይወት የመተርገፍ ዕድሉ እጅግ ጠባብ ነው። ሕፃኑ ክሌይበር ግን ይህንን የተፈጥሮ ሕግና ሳይንሳዊ ግምት በመጣስ፣ ለስድስት ቀናት ያህል ያለ ምግብና ውኃ ተቋቁሞ በመገኘቱ አጠቃላይ የነፍስ አድን ቡድኑን አስገርሟል።
የጆርዳን ሲቪል መከላከያ ባልደረቦች እንደገለጹት፣ ለሕፃኑ ወዲያውኑ የመጀመሪያ ደረጃ የሕክምና እርዳታ የተደረገለት ሲሆን፣ የወሳኝ አካላት እንቅስቃሴው በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል። በአሁኑ ወቅትም በዋና ከተማዋ ካራካስ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ልዩ የሕክምና ክትትል እየተደረገለት መሆኑን የቬንዙዌላ ብሔራዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ጆርጅ ሮድሪጌዝ አረጋግጠዋል።
ይህ ተአምር በተሰማበት በአሁኑ ወቅት፣ በሀገሪቱ ያለው አጠቃላይ ሁኔታ ግን አሁንም እጅግ አሳሳቢ ነው። ባለፈው ሳምንት በሬክተር ስኬል 7.2 እና 7.5 በሆነ ከፍተኛ መጠን የተከሰቱት መንቀጥቀጦች ያስከተሉት ውድመት በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ናሳ (Nasa) ከሳተላይት ባገኘው መረጃ መሠረት፣ በኃይለኛው መንቀጥቀጥ ሳቢያ ወደ 58,870 የሚጠጉ ሕንፃዎች ወድመዋል ወይም ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
እስካሁን ባለው መረጃ የሟቾች ቁጥር 1,943 ደርሷል ፡፡ የቆሰሉ ሰዎች ከ10,000 በላይ ሆነዋል የጠፉ (ደብዛቸው የጠፋ) በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ፍለጋ እየተደረገባቸው ነው ፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (UN) በአሁኑ ወቅት በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች አስቸኳይ የምግብ፣ የውኃ እና የመጠለያ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው በመግለጽ ዓለም አቀፍ ጥሪ አቅርቧል። በዚህ በጨለማ እና በጭንቀት በተሞላ ድባብ ውስጥ፣ የትንሹ ክሌይበር በሕይወት መተርፍ ግን ለቬንዙዌላውያን በሙሉ የትንሣኤ ያህል ትልቅ ተስፋን የጫረ ክስተት ሆኗል ያለው ቢቢሲ ነው።
ሰኔ 24 /2018 ዓ.ም
ከቬንዙዌላው ፍርስራሽ ሥር የተገኘው የሦስት ዓመቱ ሕፃን ተአምራዊ ትንሣኤ
