ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ማሊ፣ ቡርኪና ፋሶ እና ኒጀር ከአባልነት መውጣታቸው ዓለም አቀፍ የፍትህ ሂደትን ያዳክማል በሚል ስጋቱን ገልጿል።
መቀመጫውን በሄግ ያደረገው ፍርድቤቱ ፤በጦር ወንጀሎች እና በሰብአዊነት ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች ግለሰቦችን የሚከስና ለፍርድ የሚያቀርብ ተቋም ነው።
እነዚህ ሦስቱ በወታደራዊ አመራር የሚተዳደሩ የምዕራብ አፍሪካ አገራት ባለፈው ዓመት ከፍርድ ቤቱ የወጡ ሲሆን፤ ተቋሙን ‹‹በኢምፔሪያሊዝም እጅ ያለ አዲሱ የቅኝ አገዛዝ ጭቆና መሣሪያ›› ሲሉ ጠርተውታል።
ሦስቱ የቀድሞ የኤኮዋስ አባላት በ2024 የሳህል አገራት ጥምረትን መመስረታቸዉ ይታወሳል፡፡
የፍርድ ቤቱን አባል አገራት የሚወክለው የICC አባል አገራት ጉባኤ፤ በአገራቱ መውጣት መጸጸቱን ገልጿል።
ተቋሙ ባወጣው መግለጫ፤ አገራት ከፍርድ ቤቱ መውጣታቸው ‹‹የጋራ የፍትህ ፍለጋን አደጋ ላይ ይጥላል፤ እንዲሁም ወንጀል ሰርቶ ያለቅጣት የመቅረትን ባህል ለማስቆም የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ጥረት ያዳክማል›› ብሏል።
ፍርድ ቤቱ ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ እና ኒጀር በሮም ደንቡ አባልነታቸው እንዲቀጥሉ እና በአባል አገራት ጉባኤ ማዕቀፍ ውስጥ ገንቢ ተሳትፎ ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርቧል።
ከሮም ደንብ መውጣት አንድ አገር የደንቡ አባል በነበረበት ወቅት የነበሩበትን ግዴታዎች እንደማያስቀር ፍርድቤቱ አስታውሷል።
ፍርድ ቤቱ በአሁኑ ወቅት 1መቶ25 አባላት ያሉት ቢሆንም ቻይና፣ ህንድ፣ ሩሲያ፣ አሜሪካ እና እስራኤልን ጨምሮ በርካታ ዋና ዋና ኃያላን አገራት እስካሁን አባል አልሆኑም።
እስከዳር ግርማ
ሰኔ 25/2018 ዓ.ም
