ፍንዳታዎቹ የተከሰቱት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት አማኑኤል ማክሮን ያረፉበት ሆቴል አቅራቢያ መሆኑ ተገልጿል።
አንድ የደህንነት ምንጭ ለቢቢሲ እንደተናገረው ከሆነ ፍንዳታዎቹ የተከሰቱት በሁለት መሣሪያዎች አማካኝነት ነው። የሶሪያ መገናኛ ብዙኃን ደግሞ አራት የፖሊስ መኮንኖችን ጨምሮ 18 ሰዎች መቁሰላቸውን ዘግበዋል።
ማክሮን በሶሪያ ዋና ከተማ የተገኙት ከሶሪያ አቻቸው አሕመድ አል-ሻራዕ ጋር በፕሬዝዳንታዊው ቤተ መንግሥት ውይይት ለማድረግ ነው። የፕሬዝዳንቱ ባለሥልጣናት ማክሮን በሰላምና በደህና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙና የፍንዳታውን ድምፅ እንዳልሰሙ ገልጸዋል።
ማክሮን የሶሪያ ጉብኝታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ለኔቶ (NATO) ጉባኤ ወደ ቱርክ ያቀናሉ። የኤልዜ ቤተ መንግሥት (የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት) እንዳስታወቀው ጉብኝቱ “በታቀደው መሠረት ይቀጥላል”።
በከተማዋ ውስጥ ፍንዳታ መከሰቱ ከተሰማ በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የወጡ ተንቀሳቃሽ ምስሎችና ፎቶዎች በሶሪያ ዋና ከተማ ከሚገኝ አንድ ሆቴል አቅራቢያ ከቆመ ተሽከርካሪ ላይ ጥቅጥቅ ያለ ጢስና እሳት ሲነሳ ያሳያሉ።
እነዚህ ዘገባዎች በወጡበት ወቅት የሶሪያ መንግሥት ቴሌቪዥን አል-ሻራዕ ለማክሮን በፕሬዝዳንታዊው ቤተ መንግሥት አቀባበል ማድረጋቸውን ዘግቧል።
ቢቢሲ ቬሪፋይ (BBC Verify) የፍንዳታውን ተንቀሳቃሽ ምስሎች የመረመረ ሲሆን፤ ፍንዳታው የተከሰተው ፎር ሲዘንስ (Four Seasons) ከተባለው ሆቴል በግምት 125 ሜትር ያህል ርቀት ላይ፣ በዋና ከተማዋ ውስጥ በሚያልፈው ትልቅ የእግር መንገድ ላይ መሆኑን አረጋግጧል።
ሰኔ 30/2018 ዓ.ም
በሶሪያ ደማስቆ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ባረፉበት ሆቴል አቅራቢያ ፍንዳታዎች ተከስቱ 18 ሰዎች መቁሰላቸው ተነገረ
