በቻይና በተከሰተ የተፈጥሮ አደጋ የ21 ሰዎች ህይወት አለፈ

በአደጋው ሳቢያ እስካሁን ቢያንስ የ21 ሰዎች ሕይወት ማለፉ የተረጋገጠ ሲሆን፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ደግሞ ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

በሳምንቱ መጨረሻ ቻይናን የመታው ኃይለኛ አውሎ ንፋስ በሀገሪቱ ደቡባዊ እና መካከለኛው ግዛቶች ላይ ከባድ የጎርፍ መጥለቅለቅና ያልተለመደ የቶርናዶ አውሎ ንፋስ ማስከተሉ ነው የተነገረው።

በደቡባዊቷ ጓንግሺ ግዛት ዝናብ ያለማቋረጥ በመውረዱ ድንገተኛ የውሃ መጥለቅለቅ አስከትሎ፤በሰዓታት ልዩነት ውስጥ የጎርፉ ውሃ የነዋሪዎችን መኖሪያ ቤቶች የመጀመሪያ ፎቅ ሙሉ በሙሉ ማጥለቅለቁ ተገልጿል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት የጎርፉ ፍጥነት እጅግ አስደንጋጭ ከመሆኑ የተነሳ ብዙዎች ለምግብ የሚሆን እህል እንኳን ሳይይዙ ለማምለጥ ተገደዋል።

በሀገሪቱ ደቡባዊ ግዛት የተከሰተው ከባድ ዝናብ ለወንዞች መሙላት እና ለግድቦች መደርመስ ምክንያት ሆኗል ተብሏል።

አውሎ ንፋሱ ከተመታበት አካባቢ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቃ በምትገኘው ሁቤይ በተባለችው መካከለኛው የቻይና ግዛትም ጭምር ከባድ ዝናብ እና ያልተለመደ የቶርናዶ አውሎ ንፋስ ተቀስቅሷል።

በዚሁ ግዛት ብቻ 17 ሰዎች ሲሞቱ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቆስለዋል በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ተፈናቅለዋል።

የደረሰውን ከፍተኛ ውድመት ተከትሎ የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ የነፍስ አድን እና የዕርዳታ ስራዎች በሙሉ አቅም እንዲከናወኑ ጥብቅ መመሪያ አስተላልፈዋል።

ሆኖም አሁንም እየጣለ ያለው እጅግ ከባድ ዝናብ የነፍስ አድን ስራውን እያደናቀፈው እንደሚገኝ የአካባቢው ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

በቻይና በዚህ የዓመቱ ወቅት መሰል አውሎ ንፋሶች የተለመዱ ቢሆኑም፤ይህ ክስተት ግን የ2026 የጎርፍ ወቅት የመጀመሪያው ታይፉን ሆኖ ተመዝግቧል።

በአሁኑ ወቅት ‹‹ባቪ›› የተሰኘ ሌላ ኃይለኛ ሱፐር ታይፉን በፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ እየተጓዘ የሚገኝ ሲሆን፤ በሳምንቱ መጨረሻ የቻይናን ምስራቃዊ የባህር ዳርቻ ይመታል ተብሎ ይጠበቃል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

ሀናን ሸምሱ

ሐምሌ 01/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *