የኢትዮጵያን የንግድ ተወዳዳሪነት ለማረጋገጥና በሎጂስቲክስ ሰንሰለቱ ውስጥ የሚታየውን የአሰራር መዘግየት በዘላቂነት ለመቅረፍ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያገኙ 147 ባለሙያዎች በዛሬው ዕለት ተመረቁ።
የኢትዮጵያ ፍሬት ፎርዋርደርስ ኤንድ ሺፒንግ ኤጀንትስ ማኅበር (EFFSAA) ሲሰጠው የቆየውን የፊያታ (FIATA) ዲፕሎማ ስልጠና ያጠናቀቁት እነዚህ ባለሙያዎች፣ የሀገሪቱን የገቢና ወጪ ንግድ ቅልጥፍና ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራሉ ተብሎ ታምኖባቸዋል።
በኢትዮጵያ ስካይላይት ሆቴል በተከናወነው በዚህ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተገለጸው፣ የሎጂስቲክስ ዘርፉን በሰለጠነ የሰው ኃይል መደገፍ አማራጭ የሌለው አገራዊ ጉዳይ ሆኗል።
ማኅበሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ለዘርፉ ፍላጎት ተስማሚ ተደርጎ በተበጀ (Customized) የትሬዲንግ ካርድ፣ ተግባራዊና የላቀ ስልጠና የሰጠ መሆኑ የዘንድሮውን ምርቃት ልዩ ያደርገዋል ተብሏል።
የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳዊት ውብሸት በምረቃው ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ማኅበሩ እስካሁን ከ495 በላይ ባለሙያዎችን ማፍራቱን አስታውሰዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም፣ ዘርፉን ይበልጥ ለማዘመን የዲጂታል አሰራርንና የኦንላይን ስልጠናን ለመዘርጋት ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም ባለሙያዎች በማንኛውም ቦታ ሆነው እውቅና ያለው ስልጠና እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ፣ ኢትዮጵያ በ2027 ለምታስተናግደው ዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ ኮንግረስ (FIATA World Congress) ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍራኦል ጣፋ በበኩላቸው፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት በብሔራዊ የሎጂስቲክስ ስትራቴጂ ውስጥ እንደ ዋነኛ ግብ የተቀመጠ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ሀገሪቱ የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና የንግድ ፍሰቱን ለማሳለጥ በምታደርገው ጥረት፣ እንደነዚህ ያሉ በዘመናዊ እውቀት የታነጹ ባለሙያዎች መፈራታቸው ለኢንዱስትሪው ትልቅ መተማመኛ እንደሚፈጥር አስገንዝበዋል።
ይህ የፊያታ ዲፕሎማ ስልጠና በዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ መርሆዎች፣ በዕቃዎች አያያዝ፣ በጉምሩክ ሥነ-ሥርዓቶችና በፈጣን የትራንስፖርት መፍትሄዎች ላይ ያተኮረ ነው።
ሰልጣኞቹ ከተለያዩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ ከግሉ ዘርፍና ከዓለም አቀፍ ተቋማት የተውጣጡ በመሆናቸው፣ በዘርፉ ላይ የሚታየውን የባለሙያ እጥረት በስፋት ይቀርፋል ተብሎ ይጠበቃል።
በዛሬው የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አብዱልበር ሸምሱን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዘርፉ ተዋናዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በአጠቃላይ ይህ የምረቃ መርሃ-ግብር ኢትዮጵያ በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የንግድ ትስስር ውስጥ ያላትን የመደራደር አቅም ለማሳደግና ወጪና ጊዜን የሚቆጥብ ዘመናዊ የሎጂስቲክስ ሥርዓት ለመገንባት ለሚደረገው ጉዞ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑ ተመልክቷል።
ልዑል ወልዴ
ሐምሌ 07/2018 ዓ.ም
