ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነገ ለሚጀመረው ሀገራዊ ምክክር ባስተላለፉት መልዕክት፤ ውይይቱ ተራ የፖለቲካ መድረክ ሳይሆን የሀገሪቱንና የመጪውን ትውልድ እጣ ፈንታ የሚወስን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።
“አባቶቻችን በዓድዋ ለነጻነት እንደተዋደቁት ሁሉ፥ ዛሬም ሀገራችን የታሪክ አደራ የሚሸከሙ ልጆቿን ትፈልጋለች። … ሆኖም ዛሬ ኢትዮጵያ የምትሻው ጠመንጃ ያነገቡ ሳይሆን በሐሳብ ብስለት፣ በእውነትና በእውቀት የተሰናዱ የሰላም ታጋዮችን ነው” ሲሉ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው አስፍረዋል።
ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም፣ መረጋጋትና ሁለንተናዊ ብልጽግና የምትተጉ እና የኢትዮጵያ ታላቅነት ግድ የሚላችሁ ሁሉ የተዘጋጀውን ዕድል እንድትጠቀሙበት ይሁን ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
አክለውም በሰለጠነ ንግግር፣ በሰላማዊ ውይይትና አገራዊ መግባባት የገጠሙንን ፈተናዎች በሙሉ አልፈን ወደ ብልጽግና በጋራ መሻገር እንደሚቻል እና የኢትዮጵያ ማሸነፍ አይቀሬ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ሐምሌ 07/2018 ዓ.ም
