በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄድ በጀመረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መልዕክት አስተላልፈዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፤ የተገኘውን ታላቅ የምክክር ዕድል መላው ተሳታፊ በኃላፊነት ስሜትና በታላቅ አክብሮት ሊጠቀምበት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ይህ ጉባዔ በቀላሉ የማይደገም፣ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ እጅግ የገዘፈ ዓላማ ያነገበና ለአፍሪካም ምሳሌ የሚሆን ሁሉን አቀፍ መድረክ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
“አንዳንድ አጋጣሚዎች ያሻችሁን እንድትጽፉ ብዕርና ብራና ያቀብሏችኋል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ የዛሬው መድረክም የታሪክ አጋጣሚውን በአግባቡ ለመጠቀም ለሚፈልጉ ወገኖች ሀገርን የሚገነባና ለዘመናት የሚታወስ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ ሰፊ ዕድል የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል። በአንጻሩ ደግሞ ይህንን ወርቃማ ዕድል በአግባቡ ሳይጠቀሙበት በመቅረት፣ ከሚገነባ ይልቅ የሚያፈርስ የታሪክ አሻራ ጥለው የሚያልፉ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።
ቀደምት ትውልዶችና እኛ ያጣናቸውን መልካም አጋጣሚዎች ዳግም ልጆቻችን እንዳያጧቸው ለማድረግ በከፍተኛ ኃላፊነት መሥራት እንደሚገባ ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በምክክሩ ወቅት የሚነሱ ሀገራዊ ችግሮችን ወደ መልካም ዕድል በመቀየር የተሻለ ትውልድ መፍጠር እንደሚቻል ገልጸዋል።
በተጨማሪም ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተገኙ ዕድሎችን ሁሉ በአግባቡ በመጠቀም በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በወታደራዊ መስኮች በርካታ የሪፎርም ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል። ለዚህም በአብነትነት የአዲስ አበባ ከተማን ሁለንተናዊ ልማት አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉም፣ “ዛሬም በምናገኘው እያንዳንዱ ዕድል በመጠቀም ለኢትዮጵያ ብልጽግና ጠንካራ መሠረት ለመጣል በቁርጠኝነት እንተጋለን” ሲሉ አረጋግጠዋል።
ሐምሌ 08/2018 ዓ.ም
“የሀገራዊ ምክክር መድረኩን ታሪካዊ ዕድል በኃላፊነት ስሜት ልንጠቀምበት ይገባል” — ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
