‹‹ሰላም የሴቶች ድምጽ ነው›› በሚል በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ የሴቶች የሰላም ፎረም ተካሄደ

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ እኩልነት እና ልማትን ለማምጣት የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ፣ አመራር እና የሰላም ትምህርት ወሳኝ መሆናቸው ተገለጸ።

ይህ የተገለጸው ‹‹የኢትዮጵያ ሴት መሪዎች የሰላም ፎረም›› ላይ ነው።

‹‹የሰላም ትምህርትን ማሳደግ፣ የሴቶች አመራር እና ዓለም አቀፍ አጋርነት›› በሚል መሪ ቃል የተከፈተው ይህ ፎረም፣ በሴቶች ዓለም አቀፍ የሰላም ቡድን እና በኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ትብብር የተዘጋጀ ነው።

የሰላም ትምህርት እና የሴቶች ወሳኝ ሚና በፎረሙ ላይ የተነሳው ዋነኛ ነጥብ፣ ሰላም በድንገት የሚመጣ ሳይሆን በእያንዳንዱ ሰው ጥቃቅን ጥረቶች የሚገነባ መሆኑ ነው።

ሴቶች የሰላም ተጠቃሚዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ሰላምን የሚፈጥሩ እና የሚመሩ ዋነኛ አካላት መሆናቸው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን አመራሮች እንደገለጹት፤ ፌዴሬሽኑ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ የተዘረጋ ጠንካራ መዋቅር ያለው፣ ከ54 በላይ አባል ማህበራትን ያቀፈ እና ከ8.6 ሚሊየን በላይ ሴቶችን የሚወክል ተቋም ነው።

በመሆኑም ይህንን መዋቅር በመጠቀም ሴቶች በሀገሪቱ የሰላም ግንባታ እና ልማት ውስጥ ያላቸውን ቁልፍ ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ዘላቂ ሰላም በአንድ ተቋም ወይም ግለሰብ ጥረት ብቻ ሊረጋገጥ እንደማይችል የተገለጸ ሲሆን፤ ከመንግስት፣ ከትምህርት ተቋማት፣ ከሲቪል ማህበረሰብ፣ ከወጣቶች እና ከሚዲያ ጋር በጋራ በመተባበር እንዲሁም በ”ሰላም ትምህርት” አማካኝነት እንደሚገነባ አጽንኦት ተሰጥቷል።

አቤል እስጢፋኖስ

ሐምሌ 08/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *