‹‹በኤሌክትሪክ ክፍያ ላይ የታየው ለውጥ አዲስ ጭማሪ ሳይሆን ቀድሞ የተወሰነ ማስተካከያ ሂደት ነው››-የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ በደንበኞች ላይ የተደረገው የታሪፍ ማስተካከያ ክፍያ ቀደም ሲል በስትራቴጂው መሠረት የተወሰነ መሆኑን አስታዉቋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሽያጭና ደንበኞች አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ይኸይስ ስዩም ለኢትዮ ኤፍኤም 107.8 እንደገለጹት፤ በ2017 ዓ.ም መስከረም ወር ላይ የተጀመረው የታሪፍ ማሻሻያ የኅብረተሰቡን የመክፈል አቅም ባገናዘበ መልኩ በ24 የሩብ ዓመታት ተከፋፍሎ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

ይህ የታሪፍ ማስተካከያ ተቋሙ ከአራት ዓመት በኋላ የሚሰበሰበውን አጠቃላይ ክፍያ በመስከረም 2017 ዓ.ም ላይ በአንድ ጊዜ ማስከፈል የነበረበት ቢሆንም፣ የኅብረተሰቡን የመክፈል አቅም ታሳቢ በማድረግ በጥቂት በጥቂቱ ከፋፍሎ እንዲከፍል የተዘረጋ ስትራቴጂ ነው በማለት ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ያለው ታሪፍ ዝቅተኛውን የኅብረተሰብ ክፍል በልዩ ሁኔታ ለመደገፍ የመንግሥት ድጎማ የሚደረግበት ነው ያሉ ሲሆን፣ እስከ 50 ኪሎ ዋት ሰዓት የሚጠቀሙ ደንበኞች በአንድ ኪሎ ዋት ሰዓት 96 ሳንቲም ብቻ እንዲከፍሉ እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።

ዶ/ር ይኸይስ አክለውም፤ እስከ 2መቶ ኪሎ ዋት የሚጠቀም ማንኛውም ደንበኛ በትክክለኛው የታሪፍ ዋጋ ሳይሆን በድጎማ እንዲከፍል እየተደረገ ነው ብለዋል።

ደንበኞች በአንድ ወር ውስጥ በተደጋጋሚ ኃይል ሲገዙ ስለሚገጥማቸው የዋጋ ልዩነት ሲያብራሩም፤ የዋጋ አተማመን ሥርዓቱ በ30 ቀናት ውስጥ የተጠቀሙትን አጠቃላይ የኃይል መጠን በአንድ ላይ ደምሮ ስለሚያሰላው የኪሎ ዋት መጠኑ ሲጨምር ታሪፉም አብሮ እንደሚጨምር አስገንዝበዋል።

ይህንን ሁኔታ ተከትሎ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ተቋሙ በየክፍለ ከተማው ከነዋሪዎች ጋር ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቶችን እያደረገ ሲሆን፣ ባለፉት 15 ቀናት ውስጥም ከፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ለሚዲያ አካላት ስልጠና መሰጠቱ ተገልጿል።

እድላዊት ብርሃኑ

ሐምሌ 13/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *