ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ እና ኒጀር በ2032 የሚካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫን በጋራ ለማዘጋጀት ጥያቄ አቀረቡ፡፡
ይሁንና በአካባቢው ካለው የፀጥታ ስጋት አንፃር ካፍ ዕድሉን እንዳይሰጣቸው ተቃውሟቸውን የሚያሰሙ አካላትም በርክተዋል፡፡
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በ2028፣ 2032 እና 2036 የሚካሄዱትን የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች ለማዘጋጀት የሚፈልጉ ሀገራት እንዲወዳደሩ ጨረታ ማውጣቱ የሚታወስ ነው።
የማሊ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንደገለጸው የሶስቱ ሀገራት የጋራ ማመልከቻ በ”ወንድማማችነት፣ ቀጣናዊ ትስስር እና በአፍሪካ እግር ኳስ ዘላቂ እድገት” ላይ ያተኮረ ነው።
አክሎም ለአህጉራዊው ጨዋታ አዲስ ዕይታን ለማምጣት የሚያስችል “ጠንካራ እና ተአማኒነት ያለው ጥያቄ” ለማዘጋጀት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሰራ አስታውቋል።
ሦስቱ ጎረቤታሞች የሳህል ሀገራት ህብረት (AES) የተሰኘውን የፀጥታ፣ የመሠረተ ልማት፣ የንግድ እና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ስምምነት በጋራ ከመሰረቱ በኋላ ባለፈው ዓመት ከምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ECOWAS) በይፋ መውጣታቸው ይታወሳል።
ሆኖም በቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ እና ኒጄር ውስጥ ያለው የፀጥታ ሁኔታ በታጣቂ ጂሃዲስቶች ጥቃት ምክንያት አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ ያልተረጋጋ ነው።
የሦስቱ ሀገራት ወታደራዊ መንግስታት ከምዕራባውያን የደህንነት አጋሮቻቸው በመራቅ ከሩሲያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አጠናክረዋል። ይህንን የሚቃወሙ የካፍ አባል ሀገራት ደግሞ የአፍሪካ ዋንጫው እንዳይሰጣቸው ይፈልጋሉ፡፡
የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞሴፔ ከሀገራቱ የቀረበውን “የ2032ቱን የአፍሪካ ዋንጫ በጋራ እናዘጋጅ” ጥያቄ አስመልክቶ የአህጉሪቱ እግር ኳስ መሪ አካል ማመልከቻውን ከመገምገሙ በፊት የደህንነት ዋስትና ያስፈልገው እንደሆነ ተጠይቀው “ሦስቱ ሀገራት ውድድሩን ለማዘጋጀት እንደማንኛውም የአህጉሪቱ ሀገራት እኩል እድል ይኖራቸዋ” ብለዋል።
“በወታደራዊ መንግስታት በመመራታቸው ምክንያት ምንም ዓይነት አሉታዊ ተፅዕኖ ወይም ጥላቻ አይደርስባቸውም፤ ነገር ግን የሰላም እና የደህንነት ጥያቄዎች ግድ ይላል፡፡
እሱ በእርግጠኝነት ትኩረት ሰጥተን የምንገመግመው ጉዳይ ነው። ነገር ግን የ2032 አፍሪካ ዋንጫ የት እንደሚካሄድ እስካሁን የተወሰነ ውሳኔ የለም። በእርግጥ ዲሞክራሲ፣ የመናገር ነፃነት እና መደበኛ ምርጫዎች የመደራደሪያ ነጥቦች አይደሉም፤ ከዛ ይልቅ በጣም ወሳኝ ናቸው፡፡ ነገር ግን በእግር ኳሱ በኩል ለመነጋገር ወደ እነዚያ ሀገራት እጓዛለሁ” ሲሉም አብራርተዋል።
በምስጋናው ታደሰ
ሐምሌ 16/2018 ዓ.ም
