የጃፓን ኩባንያ ለሰዎች የሚሆን አዲስና ለየት ያለ ፍሪጅ አስተዋወቀ

​በጃፓን የሚገኘው ኤስ.ዲ.አር.ኤስ (SDRS) የተሰኘ ኩባንያ ለአንድ ሰው ብቻ የሚያገለግልና “ዶ ሂኤሞን ቦክስ” የተሰኘ ለየት ያለ የማቀዝቀዣ ሣጥን ለአለም አስተዋውቋል።

ይህ አዲስ ፈጠራ በይነመረብ ላይ “የሰው ልጅ ፍሪጅ” በሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶት የበርካታ ሰዎችን ትኩረት እየሳበ ይገኛል።

​የጃፓን የበጋ ወቅት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሞቀ መምጣቱ ለዜጎች ጤና አደገኛ እየሆነ በመምጣቱ በዚሁ ሐምሌ ወር ውስጥ ብቻ በቶኪዮ 48 ሰዎች በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት ለህመም ተዳርገው ወደ ሆስፒታል ገብተዋል።

ይህንን ተከተሎ ግለሰቦችም ሆኑ ኩባንያዎች የሙቀቱን አደጋ ለመከላከል የሚያስችሉ አዳዲስ መንገዶችን ሲፈልጉ የቆዩ ሲሆን፣ ኤስ.ዲ.አር.ኤስ ኩባንያ ይህንን የማቀዝቀዣ ሣጥን ለመሥራት መነሻ የሆነውም ይህ እየጨመረ የመጣው ፍላጎት ነው።

​”ዶ ሂኤሞን ቦክስ” ግልጽ የሆነ የመስታወት በር ያለው እና ለሰዎች ማቀዝቀዣነት ተብሎ የተሠራ ብረት ነክ ሣጥን ነው። ተጠቃሚዎች ወደ ውስጥ ገብተው አብሮ በተሠራው ወንበር ላይ ሲቀመጡ፣ ወደ ጭንቅላታቸው፣ አንገታቸው፣ ትከሻቸው እና ጀርባቸው የሚነፍሰውንና እስከ 5 ዲግሪ ሴልሺየስ የቀዘቀዘውን አየር ያገኛሉ።

እንደ አምራቹ ገለጻ፣ በሣጥኑ ውስጥ ለ10 ደቂቃ ያህል መቆየት የሰውነትን ሙቀት በፍጥነት ለመቀነስ እና በሙቀት ምክንያት የሚመጣን ድካም ወይም ህመም ለማስታገስ ይረዳል።

​ይህ የሰው ልጅ ፍሪጅ በውስጡ በቋሚነት 15 ዲግሪ ሴልሺየስ አካባቢ የሚሆን የሙቀት መጠን የሚጠብቅ ሲሆን፣ ሦስት የማቀዝቀዣ እና የአየር ዝውውር አማራጮች ተገጥመውለታል።

በተጨማሪም ቅዝቃዜ እንዳይበዛ ከ20 ደቂቃ በኋላ በራሱ የሚጠፋ ሲሆን፣ መደበኛ ተንቀሳቃሽ ኤሲ ከሚወስደው የኤሌክትሪክ ኃይል ግማሽ ያህሉን ብቻ በመጠቀም ረገድ ኃይል ቆጣቢ ነው ተብሏል።

መሳሪያው ምንም ዓይነት ልዩ የገጠማ ሥራ የማያስፈልገው በመሆኑ፣ አብረው በተሠሩለት እግሮች አማካኝነት በቀላሉ ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀስ ይቻላል ሲል ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል።

ሐመረ ፍሬው

ሐምሌ 16/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *