የአማራ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዳስታወቀው በመገባደድ ላይ ባለው ዓመት ከ3 ሺህ 500 በላይ ሰዎች በእብድ ውሻ በሽታ የተጠቁ ሲሆን 15 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል።
በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች በተለይም በክረምት ወቅት፣የህብረተሰቡን ጤና በእጅጉ ከሚፈትኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ የእብድ ዉሻ በሽታ መሆኑ ይነገራል፡፡
ዉሻን አስከትቦና በግቢ ዉስጥ አስሮ መያዝ ብዙም ትኩረት በማይሰጥበት ሁኔታ ዉሾች ለበሽታ የመጋለጣቸዉና በዚያኑ ያህል ህብረተሰቡ በበሽታዉ እንዲጠቃ የማድረግ እድላቸዉ የሰፋ ሆኖ ይታያል፡፡
በአማራ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠሪያ ከእንስሳት ወደ ሰዉ ተላላፊ በሽታዎች ጉዳይ ሃላፊ የሆኑት አቶ ሃይሉ አያሌዉ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት፣በክልሉ በዚሁ በሽታ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር ከፍ ያለና ከባድ የህብረተሰብ የጤና ችግር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህ ዓመት ብቻ እስከ ግንቦት ወር መጨረሻ ድረስ 15 ሰዎች ከዚሁ በሽታ ጋር በተያያዘ ሲሞቱ ከ 3 ሽህ 500 በላይ የሚሆኑት ደግሞ መጠቃታቸዉን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ በገጠርም ይሁን በከተማ ዉሻዎች በሰዓቱ ክትባት እንደማያገኙ የሚናገሩት ሃላፊዉ፣ይህ የሆነዉ ደግሞ ባለዉ ዝቅተኛ ግንዛቤ መሆኑን ያናገራሉ፡፡
ለክትባት ለአንድ ዉሻ 15 ብር ብቻ የሚጠየቅ ቢሆንም ከነጭራሹ የማስከተቡ ሃሳብ በህብረተሰቡ ዘንድ የለም ሲሉም ያነሳሉ፡፡
ከዚህ ባሻገርም ዉሻን በግቢ ዉስጥ አስሮ መንከባከብ አልተለመደም፤ይህም በርካታ ዉሻዎች በከተሞች ሳይቀር እንዲበረክቱ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
በዚህ መሰረትም በእብድ ዉሻ በሽታ የተለከፋ ሰዎች ቁጥራቸዉ ከዚህ ከፍ ሊል እንደሚችል በመግለጽ ህብረተሰቡ መሰል ችግር ሲገጥመዉ ወደ ጤና ተቋማት ከመሄድ ይልቅ ለባህላዊ ህክምናዎች ቅድሚያ እንደሚሰጥም አንስተዋል፡፡
በሽታዉን ለመከላከል ቀድሞ ተመራጩ ጉዳይ ዉሻን ማስከተብ ነዉ፤ አንዳንድ ጊዜም የእብድ ውሻ በሽታ ታካሚው የበሽታውን ምልክቶች ማሳየት ከመጀመሩ በፊት ህክምናውን ካገኘ በሽታውን ሊከላከል እንደሚችል ይጠቀሳል፡፡
ሀላፊዉ እንደሚሉት ታዲያ፣ ህብረተሰቡ ዉሾቹን እንዲያስከትብ፣በአግባቡ እንዲንከባክብና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት እንዲስፋፉ ቢደረግ በሽታዉን በመከላከል ረገድ የተሻለ ለዉጥ ይመጣል ሚል እምነት እንዳላቸዉ ነግረዉናል፡፡
ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8
በሙሉቀን አሰፋ
ሰኔ 18 ቀን 2012 ዓ.ም
