በስሜት እና በድንጋጤ ውስጥ ያሉ ተጎጂዎችን ወዲያውኑ ቃለ-መጠይቅ ማድረግ ተጨማሪ የሥነ-ልቦና ጉዳት ያስከትላል ተብሏል፡፡
ይህ የተባለዉየኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር (ኢሕባሴማ) ከፈረንሳይ ኤምባሲ ጋር በመተባበር የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በፆታ ተኮር ጥቃቶች እና በተጎጂዎች ሥነ-ልቦና ላይ ያተኮረ ዘገባን እንዴት ማቅረብ እንዳለባቸው የሚያስነዝብ የሁለት ቀን ሥልጠና በሰጠበት ወቅት ነዉ፡፡
የሥልጠናው ዋና ዓላማ ጋዜጠኞች ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች እና ሕፃናት ሥነ-ልቦና ያማከለ፣ ከሁለተኛ ደረጃ የሥነ-ልቦና ጉዳት የጸዳ እና የሙያ ሥነ-ምግባርን የጠበቀ ዘገባ እንዲያቀርቡ ለማስቻል እንደሆነ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር የፕሮግራም ኦፊሰር ሮዛ አበበ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት የፆታ ተኮር ጥቃቶች ዘገባዎች በማኅበራዊ ሚዲያ እና በመገናኛ ብዙኃን በቀላሉ ትኩረት የሚያገኙ እና የመነጋገሪያ ርዕስ የሚሆኑበት ሁኔታ አለ ሆኖም ግን ዘገባዎች ከትኩረት መሳብ ባሻገር በተጎጂዎች ህይወት እና በማኅበረሰቡ ላይ የሚያደርሱትን ሥነ-ልቦናዊ ተፅዕኖ ማገናዘብ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ጋዜጠኞች ጥቃት የደረሰባቸውን ወገኖች ስም እና ማንነት ሲዘግቡ ፍቃደኝነታቸውን ማረጋገጥ፣ ከጥቃት አድራሽነት ነፃ ያደረገ አቀራረብን መከተል እና ተጠያቂነትን ያማከለ ዘገባ መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
በሥልጠናው ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የሥነ-ልቦና ባለሙያዉ ሞገስ ሀብተማሪያምበበኩላቸው፤ በስሜት እና በድንጋጤ ውስጥ ያሉ ተጎጂዎችን ወዲያውኑ ቃለ-መጠይቅ ማድረግ ተጨማሪ የሥነ-ልቦና ጉዳት እንደሚያስከትል ገልጸዋል።
በመሆኑም ጋዜጠኞች ዘገባዎችን ሲያዘጋጁ ተጎጂዎች ረጋ ባሉበት እና ስሜታቸውን በተቆጣጠሩበት ወቅት፣ በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ኢንተርቪው ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸው፤ ይህም ራሳቸውን ጋዜጠኞችን እና ማኅበረሰቡን ከሥነ-ልቦና ጫና እንደሚጠብቅ አስረድተዋል።
ባለፉት 31 ዓመታት የሴቶች እና ሕፃናትን መብት ለማስከበር ሲሠራ የቆየው የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር፤ በነፃ የሕግ ድጋፍ፣ በፖሊሲ ተሟጋችነት እና በነፃ የስልክ መስመር 7711 አማካኝነት በሁሉም ክልሎች አገልግሎት መስጠቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ሀና ሰይፉ
ሐምሌ 24/2018 ዓ.ም
