በኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከሚላኩ እና ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ ምርቶች መካከል ያለው ከፍተኛ የገንዘብ አለመመጣጠን፣ በሀገሪቷ የመክፈል አቅም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን የገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሞቱማ ተመስገን ተናግረዋል።
ዋና ስራ አስኪያጁ ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳመለከቱት፤ ይህንን የንግድ ሚዛን መዛባት ለመቅረፍ በማኑፋክቸሪንግ እና በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል።
በተለይም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች መተካት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
አቶ ሞቱማ አክለውም፣ የውጭ ኢንቨስተሮች በሀገር ውስጥ ምርቶች ላይ አተኩረው እንዲሰሩ ለማድረግ አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን ማሟላት እና የአገልግሎት አሰጣጥን ማቀላጠፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት በገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን 1 ቢሊዮን ዶላር ካፒታል ያስመዘገቡ 115 ያህል ባለሀብቶች ገብተው እየሰሩ እንደሚገኝ የተናገሩት ዋና ስራ አስኪያጁ፤ በዞኑ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ ትኩረት በማድረግ እንደ ሴራሚክ እና ብረት ያሉ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማረት መቻሉን አስረድተዋል።
ሰላማዊት ዲታ
ሐምሌ 24/2018 ዓ.ም
